ለጥቂት ደቂቃዎች ወደ ጠፈር ለመጓዝ የአንድ ወንበር የጨረታ ዋጋ ከ2 ነጥበ 4 ሚሊዮን ዶላር አለፈ
ወንበሩን በመግዛት የመጀመሪያውን የጠፈር ጉዞ ትኬት በእጃቸው ማስገባት ለሚፈልጉ የ1 ወር ጊዜ አላቸው ተብሏል
‘ኒው ሼፓርድ’ ሮኬት ተጓዦችን በመያዝ በአውሮፓውያኑ የፊታችን ነሃሴ ወር ወደ ጠፈር እንደምትጓዝ ይጠበቃል
ወደ ጠፈር ተጓዦችን አሳፍሮ ለመሄድ በ‘ብሉ ኦሪጅን’ ተቋም በወጣው ጨረታ የአንድ ወንበር የጨረታ ዋጋ ከ2 ነጥበ 4 ሚሊን ዶላር ማለፉ ተነግሯል።
የአሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ የጠፈር ምርምር ተቋም ‘ብሉ ኦሪጅን’ ፣ ‘ኒው ሼፓርድ’ በተባለችው መንኮራኩር ወደ ጠፈር ለጥቂት ደቂቃዎች የሚደረገው ጉዞ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ጨረታ መውጣቱ ይታወሳል።
ወደ ጠፈር መጓዝ ለሚፈልግ ሰው ወንበር እንዲገዛ ጨረታ የወጣ ሲሆን ፤ አሁን ላይ የአንዱ ወንበር የጨረታ መነሻ ዋጋ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ማለፉ ነው የተሰማው።
ወደ ጠፈር ለሚደረገው ጉዞ ወንበሩን መግዛት እና የመጀመሪያውን ወደ ጠፈር የሚደረገውን ትኬት በእጃቸው ማስገባት ለሚፈልጉ ሰዎች የአንድ ወር ጊዜ እንዳላቸውም ነው የተነገረው።
‘ኒው ሼፓርድ’ ሮኬት ከጠፈርተኞች ውጪ የመጀመሪያ ተጓዦችን በመያዝ በአውሮፓውያኑ የፊታችን ነሃሴ 20/2021 ወደ ጠፈር እንደምትጓዝ ይጠበቃል።
ወደ ጠፈር የሚጓዙ ግለሰቦችም የመሬት ስበት ዜሮ በሆነበት ስፍራ ላይ ለደቂቃዎች እንዲንሳፈፉ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡ የጠፈርን አፈጣጠር እና ስነምህዳር እንዲመለከቱ ይደረጋልም ተብሏል።
‘ብሉ ኦሪጅን’ በመጀመሪያው ዙር ከ 136 ሀገራት ከ 5,200 በላይ ተጫራቾችን መቀበሉን ገልፆ ፣ ይህ ዙር የታሸገ በመሆኑ የጨረታውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ይፋ አላደረገም።
ሮኬቷ በአንድ ጊዜ 6 ሰዎችን ይዛ እንድትወነጨፍ ተደርጋ ነው የተዘጋጀችው።