ማዕከሉ በሶስት አመታት ውስጥ ይገነባል ተብሏል
ኢትዮጵያ የሳተላይት መገጣጠሚያ ማዕከልን ልትገነባ ነው
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳተላይት ፍብረካ፣መገጣጠሚያ እና ሙከራ ማዕከል በኢትዮጵያ ሊገነባ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የፕሮጀክት ትግበራው ሶስት ዓመታትን የሚፈጅ ነው ያሉት በኢንስቲትዩቱ የስፔስ ኢንጂነሪንግ ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ ዶ/ር ይሹሩን አለማየሁ ፕሮጄክቱ እስከ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ሳተላይቶችን ለማምረት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
ከኢንስቲትዩቱ የፌስቡክ ገጽ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ ፕሮጄክቱ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥረ ግቢ ዉስጥ የሚገነባ ነው፡፡
ፕሮጄክቱን ለመገንባት የሚያስችለው ስምምነትም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሮች በተገኙበት በኢንስቲትዩቱ እና በዩኒቨርሲቲው መካከል ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱ በዋናነት በኤሮስፔስ ምህንድስና ዘርፍ የጋራ ምርምር ለማካሄድ፤ በዘርፉ በ2ኛና 3ኛ ዲግሪዎች ለማስተማር እንዲሁም ለሃገር እድገት ጠቃሚ በሆኑ ሌሎች የስፔስ ሳይንስ ምርምር ዘርፎች ዙሪያ ተባብሮ ለመስራት ያስችላል ተብሏል፡፡
50 ሚሊዬን ዩሮ ይፈጃል የተባለ ሲሆን 25 ሚሊዬኑ በአዉሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ፤ የተቀረዉ ደግሞ የሳተላይት ቴክኖሎጂ ማምረቻ የሚሆኑ ማሽኖችን በሚያቀርበው በፈረንሳዩ አርያን ግሩፕ እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፍን ነው፡፡
ፕሮጄክቱ እውን የሚሆን ከሆነ በምስራቅ አፍሪካ በዓይነቱ የመጀመሪያው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡