አዛውንት ገጭቶ የገደለው በግ የሶስት ዓመት እስር ተፈረደበት
ሙክቱ በግ አንዲት አዛውንትን ገጭቶ መግደሉን ተከትሎ የበጉ ባለቤት ካሳ እንዲከፍል ተፈርዶበታል

የበጉ ባለቤት ለተጎጂ ቤተሰቦች አምስት ላሞች ካሳ ለመክፈል መስማማቱ ተገልጿል
አዛውንት ገጭቶ የገደለው በግ የሶስት ዓመት እስር ተፈረደበት፡፡
የሰው ልጅ ለገደላቸው እንስሳት ሁሉ በህግ ቢጠየቅ እስር ቤቶች በሰዎች ይሞሉ ነበር፡፡ ከወደ ሱዳን ያጋጠመው ክስተት ግን ለየት ያለ ነው፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በጎረቤት ሀገር ሱዳን ምስራቃዊ የሀገሪቱ አካባቢ በምትገኘው ሩምቤክ ተብላ በምትጠራ አካባቢ አንድ ሙክት በግ አንዲት አዛውንት ላይ ባደረሰው ጉዳት ከቀናት ህመም በኋላ ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል፡፡
አዛውንቷ በበጉ ግጭት ምክንያት የጎድን እና ዳሌ አጥንታቸው ተጎድቷል የተባለ ሲሆን በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡
በሀገሪቱ የባህላዊ አስተዳድር ወይም ሽምግልና መሰረት የበጉ ባለቤት ሀላፊነት እንዲወስድ ተደርጓል የተባለ ሲሆን ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል እንደተስማማ ተገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን በጉ አዛውንቷን ሲገጭ ባዩ የአይን እማኞች አማካኝነት የሶስት ዓመት እስር የተላለፈበት ሲሆን ቅጣቱን በወታደራዊ ካምፕ ይጨርሳል መባሉን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
በግጭቱ ምክንያት ህይወታቸው ላለፈው አዛውንት የበጉ ባለቤት አምስት ላሞችን በካሳ መልክ ለመክፈል መስማማቱም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ወንጀለኛ ነው የተባለው ይህ በግም የሶት ዓመት የእስር ጊዜውን ሲጨርስ ለተጎጂ ቤተሰቦች ተላፎ ይሰጣልም ተብሏል፡፡