ሩሲያ የአሜሪካ ሚሳኤሎች በግዛቷ ላይ ጥቅም ላይ ከዋሉ 'ተጨባጭ' ምላሽ እንደምትሰጥ ዛተች
በሩሲያ በግዛቷ ጥቃት ከተፈጸመ "አሜሪካና አጋሮቿ በጦርነቱ በቀጥታ እንደተሳተፉ ይቆጠራል” ብላለች
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን ከአሜሪካ በተላኩላት ሚሳኤሎች ሩሲያን እንድትመታ ፈቃድ ሰጥተዋል
ሩሲያ የአሜሪካ ሚሳኤሎች ግዛቷን ለማጥቃት ጥቅም ላይ ከዋሉ 'ተጨባጭ' ምላሽ እሰጣለሁ ስትል አስጠንቅቃለች።
የአሜሪካውፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን ከአሜሪካ በተላኩላት ሚሳኤሎች በሩሲያ ላይ ጥቃት እንደትፈጽም መፍቀዳቸው በትናንትናው እለት ተሰምቷል።
ባይደን በጥር ወር ዋይትሃውስን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ዩክሬን ለወራት ስታነሳው የነበረውን ከድንበሯ ውጭ (በሩሲያ መሬት ውስጥ) የአሜሪካን ሚሳኤሎች የመጠቀም ጥያቄ ነው የተቀበሉት።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ “እንዲህ አይነት ጉዳዮች በይፋ አይገለጹም፤ ሚሳኤሎቹ ራሳቸው ይናገራሉ” በማለት ከዋሽንግተን ፈቃድ ማግኘታቸውን በተዘዋዋሪ አረጋግጠዋል።
ይህንን ተከትሎም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ የአሜሪካ ሚሳኤሎች የሩሲያ ግዛትን ለማጥቃት ጥቅም ላይ ከዋሉ ሀገሪቱ 'ተጨባጭ' ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ አክሉም በሩሲያ በግዛት የአሜሪካ ሚሳዔሎችን በመጠቀም ጥቃት ከተፈጸመ "አሜሪካና አጋሮቿ በጦርነቱ ቀጥታ ተሳትፎን ይወክላል” ብሏል።
የፕሬዝዳንት ፑቲን ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየትም፤ “አሜሪካ በእሳቱ ላይ ቤንዚን እያርከፈከፈች ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት ባይሰጡም፤ ከዚህ ቀደም ምዕራባውያን ሀገራት መሰል ውሳኔ ካሳለፉ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት(ኔቶ) በዩክሬኑ ጦርነት “በቀጥታ እንደተሳተፈ ይቆጠራል”፤ የኒኩሌር ጦርነትም ሊያስነሳ ይችላል በሚል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው።
ዩክሬን እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ የአሜሪካ “ATACMS (የጦር ታክቲካል ሚሳኤል ሲስተም) እንዲሁም ተመሳሳይ ርቀት ማጥቃት የሚችሉ የፈረንሳይ እና የእንግሊዝ ሚሳኤሎች የታጠቀች ሲሆን፤ ነገር ግን ምእራባውያን ዩክሬን በሚሳዔሎቹ ሩሲያን እስዳትመታ ሲከለክክሉ ቆይተዋል።
አሜሪካ ሚሳዔሎቿ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የፈቀደችው፤ አሜሪካ እስከ 300 ኪሎሜትር ድረስ የሚጓዙት ሚሳኤሎች ሩሲያን ለማጥቃት እንዲውሉ የፈቀደችው ሞስኮ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በዩክሬኑ ጦርነት እንዲሳተፉ መፍቀዷን ተከትሎ ነው ተብሏል።
የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በነሃሴ ወር ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ክልል የገቡትን የዩክሬን ወታደሮች ለማስወጣት በቅርብ ቀናት ውስጥ መጠነሰፊ ውጊያ እንደሚጀምሩ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ዩክሬን በኩርስክ ክልል ከ11 ሺህ በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እንደሚገኙ ማስታወቋ ይታወሳል።
የፕሬዝዳንት ባይደን ውሳኔ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ለኬቭ የላኩት “ስቶርም ሻዶው” የተሰኘው ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል የሩሲያን ድንበር ተሻግሮ ጥቃት ለማድረስ እንዲውል ፈቃድ መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ ስለመሆኑ ተዘግቧል።
ይሁን እንጂ ለንደንም ሆነች ፓሪስ ለባይደን ውሳኔ እስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም።
የጀርመኑ የጥናት ተቋም ኬል ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው አሜሪካ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለኬቭ ከ55 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጋለች።