የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል በግብጽ የአየር ጥቃት እየተፈጸመብኝ ነው ሲል ከሰሰ
ጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ የሀገሪቱ ጦር ዋና ከተማዋን ለመቆጣጠር በከፈተው መጠነ ሰፊ ዘመቻ ግብጽ እየተሳተፈች ነው ብለዋል
ካይሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ ክሱን አጣጥላለች
የሱዳን ብሔራዊ ጦር በቅርብ ሳምንታት በከፈተው መጠነ ሰፊ ውግያ የግብጽ አየር ሀይል እየተሳተፈ እንደሚገኝ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ዋና አዛዥ ጄነራል ሃምዳን ዳጋሎ ተናግረዋል፡፡
በጄነራል አብዱልፈታህ አልቡራሀን የሚመራው የሱዳን ጦር ዋና ከተማዋ ካርቱምን ድጋሚ ለመቆጣጠር ባስጀመረው በአየር ሀይል የታገዘ ውግያ የተለያዩ ስፍራዎችን ድጋሚ እየተቆጣጠረ እንደሚገኝ እየተነገረ ነው፡፡
ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ላይ በሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶች የገብጽ አየር ሀይል ተሳትፏል በሚል የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አዛዥ ሀምዳን ዳጋሎ ክስ አቅርበዋል፡፡
ትላንት ምሽት ተቀርጾ በተላለፈው የጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ የቪድዮ መልዕክት ካይሮ በአየር ጥቃቱ ከመሳተፍ ባለፈ ለሱዳን ጦር የድሮን ጦር መሳርያ እና ስልጠና እየሰጠች እንደምትገኝ ገልጿል፡፡
የአሜሪካ ይሁንታ ሳይኖርበት ግብጽ በጥቃቱ እንደማትሳተፍ የገለጹት ሄሜቲ፥ የኢትዮጵያ የትግራይ ተወላጆች ፣ የኤርትራ ፣ የአዘርባጃን እና የዩክሬን ቅጥረኛ ወታደሮች በጦርነቱ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ኢራንም ብሄራዊ ጦሩን በመደገፍ እንደተሰለፈች መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ካይሮ ለቀረበባት ወቀሳ በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል በሰጠችው ምላሽ የግብጽ አየር ሀይልም ሆነ ጦር በሱዳኑ ጦርነት ምንም አይነት ተሳትፎ የለውም ስትል አስተባብላለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አለም አቀፉ ማህበረሰብ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ያቀረበባትን ክስ በገለልተኛ አካል እንዲያጣራ ጥሪ አድርጋለች፡፡
የሱዳን ጦር እና የጄነራል አብዱልፈታህ አልቡራሀን የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች የሚነገርላት ግብጽ ሁለቱን ተዋጊዎች ለማስማማት ጥረት በሚያደርገው አሜሪካ እና ሳኡዲ አረብያ የሚገኙበት የአደራዳሪ ቡድን ውስጥ ትሳተፋለች፡፡
በ2024 መጀመርያ ላይም የሁለቱ ተፋላሚዎች ተወካዮች በግብጽ ተገናኝተው መክረው እንደነበር ይታወሳል፡፡
18 ወራትን ባስቆጠረው የሁለቱ ጄነራሎች ውግያ ምድር ላይ እየተካሄዱ ከሚገኙ ውግያዎች በርካታ ንጹሀንን ከቀያቸው በማፈናቀል ቀዳሚው ነው፡፡
ምንም እንኳን ጄነራሎቹ ቢያስተባብሉትም ተዋጊዎቻቸው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የጦር ወንጀሎችን በመፈጸም በተደጋጋሚ ይወቀሳሉ፡፡
ከሱዳን 18 ክልሎች ከግማሽ በላዩን ተቆጣጥሮ የሚገኘው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በቅርቡ በተከፈተበት መጠነ ሰፊ ዘመቻ በዋና ከተማዋ አቅራቢያ ከሚገኙ ሲናር ክልል እና ጄበል ሞያ ከተሰኙት ስትራቴጂካዊ አካባቢዎች በማፈግፈግ ላይ ይገኛል፡፡