ስዊዝ ቦይ ላይ ተሰንቅራ የነበረችው ኤቨርጊቭን መርከብ እስካሁን ግብፅን አልለቀቀችም
የስዊዝ ቦይ ባለሰልጣን ለደረሰበት ኪሳራ እና ስም መጥፋት 900 ሚሊየን ዶላር ካሳ ጠይቋል
የተጠየቀው የካሳ መጠን የተጋነነ ከመሆኑ በላይ ግብጽ መርከቧን ማገቷ የመርከቧ ባለቤት አስቆጥቷል
የታይዋን ኤቨርግሪን የባህር ትራንስፖርት ኩባንያ ንብረት የሆነችው እና የ224 ሺ ቶን ክብደት ያላት ኤቨርግሪን መርከብ ከ21 ቀን በፊት መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር በከፍተኛ ንፋስ በድንገት ተመትታ ለ6 ቀናት ስዊዝ ቦይን የዘጋችው።
ስዊዝ ቦይን ዘግታ የነበረችው ኤቨር ግሪን መርከብ ወደ ሆላንዷ ሮተርዳም ለማቅናት ከቀይ ባህር ወደ ሜዲተራኒያን ባህር በምትሻገርበት ወቅት እንደነበር በወቅቱ መገለጹ አይዘነጋም፡፡
ይህች መርከብ የዓለማችን 10 በመቶ ንግድ መተላለፊያ የሆነውን ስዊዝ ቦይን በመዝጋቷ ከ400 በላይ የዓለማችን መርከቦች እንቅስቃሴ ተገትቶ ቆይቷል።
የስዊዝ ካናል ባለሰልጣን ባደረገው ጥረት መርከቧን እንድትንቀሳቀስ ቢያደርግም ለደረሰበት ኪሳራ እና ስም መጥፋት 900 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ጠይቋል።
ባለሰልጣኑ ካሳው እስኪከፈለው ድረስ ይህችን መርከብ ከስዊዝ ካናል ዘወር አድርጎ በአንድ ባህር ላይ አግቶ ማስቀመጡን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
መርከቧ በስዊዝ ካናል ላይ ያደረሰችው ጉዳት ለግብጽ ካሳ እስካልተከፈለ ድረስ እንደማትለቀቅም ተገልጿል።
ይሁንና በእንግሊዝ ያለው የኤቨርጊቭን መርከብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ግብጽ የጠየቀችው የካሳ ክፍያ መጠን የተጋነነ እና ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።
የስዊዝ ካናል ባለስልጣን የጠየቀው የካሳ መጠን የተጋነነ ከመሆኑ በላይ መርከቧን ማገቱ እንዳስቆጣቸውም የመርከቧ ባለቤት አስታውቋል።
የመርከቧ ኢንሹራንስ ኩባንያ መርከቧ በስዊዝ ካናል ላይ ላደረሰችው ጉዳት ካሳ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ፣ ኩባንያው ካሳ ለመክፈል ለግብጽ ጥያቄ ቢያቀርብም የስዊዝ ካናል ባለሰልጣን ውድቅ እንዳደረገበት ገልጿል።
በመሆኑም ኩባንያው ጉዳዩን በፍርድ ቤት ክርክር ለመቋጨት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።