የግብፁ ስዊዝ ቦይ 1 ቢሊየን ዶላር ካሳ ያስፈልገኛል አለ
የግብፁ የስዊዝ ቦይ መተላለፊያው ለአንድ ሳምንት ገደማ ‘ኤቨር ጊቭን’ በተሰኘ መርከብ ተዘግቶ ቆይቷል
የዓለማችን 12 በመቶ የሚሆነው የንግድ መርከብ በስዊዝ ቦይ በኩል ነው የሚተላለፈው
የግብፁ የስዊዝ ቦይ መተላለፊያው ለአንድ ሳምንት ገደማ ‘ኤቨር ጊቭን’ በተሰኘ መርከብ ተዘግቶ በቆየበት ወቅት ለደረሰበት ጉዳት ካሳ ያስፈልገኛል አለ።
የስዊዝ ቦይ ባለስልጣን በመርከቧ ምክንያት መተላፊያው ተዘግቶ በቆየበት ወቅት ለታጣው ገቢ ማካካሻ የሚሆን 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ካሳ ያስፈልገኛል ማለቱን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የስዊዝ ቦይ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኦስማን ራቢ በሀገሪቱ ከሚገኝ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የሰዊዝ ቦይ ተዘግቶ በቆየበት ወቅት ሀገሪቱ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ማጣቷን እና ግብፅ ይህንን የመጠየቅ ሙሉ መብት አላት ብለዋል።
ባለስልጣኑ ካሳውን የሚጠይቀው መርከቧ የስዊዝ ቦይን በዘጋችበት ወቅት ለታጣው ገቢ ብቻ ሳይሆን፤ መረከቧን ከገባችበት ቅርቃር ለማውጣት ለተጠቀማቸው የመቆፈሪያ መሳሪዎች እና ጎታች መርከቦች ወጪን ለመሸፈን የሚውል መሆኑንም አስታውቋል።
የግብፁ ስዊዝ ቦይ መተላለፊያ ለስድስት ቀናት ተዘግቶ በመቆየቱ 422 መርከቦች ለማለፍ በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ የስዊዝ ቦይ መከፈትን ተከትሎም መርከቦች ማለፍ መጀመራቸውንም ባለስልጣኑ አስታቋል።
አስከ ነገ ድረስም በመተላለፊያ ምክንያት ቆመው የነበሩ 422ቱም መርከቦች በስዊዝ ቦይ በማለፍ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዋና ስራ አስፈፃሚው ኦስማን ራቢ ገልጸዋል።
በዓለም ላይ እጅግ ከተጨናነቁ የንግድ መርከብ መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው የግብፁ ስዊዝ ቦይ መተላለፊያ ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ በታይዋን ኩባንያ ‘ኤቨርግሪን ማሪን’ በሚተዳደረው ‘ኤቨር ጊቭን’ በተሰኘ መርከብ ለ6 ቀናት ተዘግቶ መቆየቱ ይታወሳል።
የስዊዝ ቦይን የዘጋው ‘ኤቨር ጊቭን’ የተሰኘ መርከብ የ224 ሺህ ቶን ክብደት ፣ 400 ሜትር ርዝመት እና 59 ሜትር ስፋት ያለው ነው።
የስዊዝ ቦይ ሜዲትራኒያን ባህርን ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኝ መተላለፊያ መስመር ሲሆን፣ እሲያ እና አውሮፓ በአቋራጭ የሚገናኙበት መስመርም ነው።
የዓለማችን 12 በመቶ የሚሆነው የንግድ መርከብ በዚሁ በስዊዝ ቦይ በኩል እንደሚተላለፍም መረጃዎች ይጠቁማሉ።