የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አማጺያን በሚንቀሳቀሱበት በደቡብ ኮረዶፋን ጉብኝት አደረጉ፡፡
በሽግግር ላይ የምትገኘው ሱዳን በሲቪልና በወታደራዊ አስተዳደር ስር መተዳደር ከጀመረች ወራት ተቆጥረዋል፡፡
ወታደራዊ የሽግገር ምክር ቤቱና ተቃዋሚዎች በደረሱት ስምምነት መሰረትም ሱዳን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መርጣለች፡፡
የምጣኔ ሃብት ምሁሩና አዲሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በሃገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲመጣ፣ ሰላም እንዲሰፍን ብሎም ሱዳን በአገር ውስጥም በውጭም ያላት ገጽታ እንዲለወጥ ለማድረግ እንደሚሰሩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎ ሱዳን ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻሻል ለማድረግም ብዙ መስራታቸው ተነገሯል፡፡
ከውጭ አገራት ባለፈም በሱዳን ውስጣዊ ሰላም ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሱዳን ፖለቲካ ትልቅ ስም ያለው የሳውዝ ፒፕል ላይብሬሽን ሙቭመንት ይዞታ በሆነውና በደቡብ ኮርዶፋን በሚገኘው ኩአዱ ጉብኝት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
ጉብኝቱ ደግሞ ለርጅም ጊዜ በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆየው ይህ ፓርቲ ወደ ሰላም እንዲመጣና በአገሪቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰላማዊ ንግግር እንዲኖር ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
አብደላ ሃምዶክ ወደ ስፍራው ያቀኑት በሱዳን ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዶናልድ ቡዝ፣ ከብሪታኒያ አምባሳደር ኢፍራን ሲዲቅ፣ ከኖርወይ መልዕክተኛ ኢድሬ ስቴንሰን እና ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይርክተር ዴቪድ ቢሰሌይ ጋር በመሆን ነው፡፡
ከፍተኛ የሱዳን ባለስልጣን ወደ ስፍራዉ ሲያቀና ከ2011 በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የመጀመሪያ መሆናቸው ተገልቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ሲደርሱ ደማቅ አቀባባል እንደተደረገላቸው የተገለጸ ሲሆን ውይይትና ንግግር የሱዳን የፖለቲካ ባህል እንዲሆን መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
የንቅናቄው መሪ አብዱላዚዝ ኢል ሂሉ በበኩላቸው ወደ ሰላማዊ ንግግር ለመምጣት መዘጋጀቱንም የሱዳን ባህልና መረጃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታወቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ እንዳሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኩአዱ ግብኝት ለሱዳን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የንቅናቄው መሪ ውይይት ማድረጋቸውንም የሱዳን ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሳውዝ ፒፕል ላይብሬሽን ሙቭመንት መሪ አብዱላዚዝ ኢል ሂሉ ወደ ካርቱም እንዲመጡ መጋበዛቸውም ተሰምቷል፡፡
አብደላ ሃምዶክ በሱዳን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ የአገሪቱ ዜጎች ለብሄራዊ እንድነትና መግባባት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሳውዝ ፒፕል ላይብሬሽን ሙቭመንት በሱዳን ብሉናይልና ደቡብ ኮረዶፋን ግዛት የሚንቀሳቀስ ንቅናቄ ነው፡፡
ፓርቲው ደቡብ ሱዳን በ2011 በውሳኔ ህዝብ ከሱዳን ስትነጠል የሳውዝ ፒፕል ላይብሬሽን ሙቭመንት ግን ሱዳን ውስጥ እየታገለ የቆየ ንቅናቄ ነው፡፡