ወታደሮቿ ኢራቅን ለቀው ይወጣሉ መባሉን አሜሪካ አስተባበለች
የሀገሪቱ መከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎን የአሜሪካ ወታደሮች ኢራቅን ለቀው ይወጣሉ መባሉን አስተባብሏል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ የፔንታጎን ዋና ጸሃፊው ማርክ ኢስፐር ሃገራቸው ወታደሮቿን ከኢራቅ የማስወጣት ዕቀድ እንደሌላት ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ግን ከሰሞኑ የውጭ ሃገራት ወታደሮች ኢራቅን ለቀው እንዲወጡ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ወስነዋል በሚል እነ ሮይተርስ ጭምር ዘግበው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
የረጅም ጊዜ ተቃናቃኞቹ ቴህራንና ዋሽንግተን በፕሬዘዳንት ትራምፕ ትእዛዝ የኢራኑ መታደራዊ አዛዥ ካሴም ሱሌማኒ ኢራቅ ውስጥ ከተገደሉ በኋላ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡
ጄነራል ካሴም ሱሌማኒ በኢራቅ ዉስጥ ከመንፈሳዊ መሪው አያቶላህ አሊ ካሚኒ ቀጥሎ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የኢራን ጄነራል በአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ በኢራቅ ምድር ከተገደሉ በኋላ ነበር ኢራቅ በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ወታደሮች እንዲወጡ በሀገሪቱ ፓርላማ በኩል የወሰነችው፡፡
ቴህራን የበቀል እርምጃ የምትወስድ ከሆነ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማእቀብ እንደምትጥልና የኢራንን ቅርሶችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት እንደምትሰነዝርም አስታውቀም ነበር፡፡