ዶ/ር ፈቀደ ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት አዲስ ነው የተባለ የልብ ህክምናን በማስተዋወቅም ይታወቃሉ
ከቶንሲል እና ተያያዥ ህመሞች ጋር በተያያዘ የሚመጡ በተለይም ቦርቀው ባልጠገቡ ህጻናት ላይ የሚያጋጥሙ የል ህመሞችን በማከም ይታወቃሉ በሚል አል ዐይን አማርኛ ከአንደበታቸው ጠይቆ የዘገበላቸው ዶ/ር ፈቀደ አግዋር ህክምናው በአብዛኛው ልብና ሳንባ ቆሞ የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
ልብ እና ሳንባ የህይወትን፤ የእስትንፋስንም ያክል ናቸው፡፡ እነሱ ቆመው ለአፍታ መቆየቱ እንኳን ይቸግራልና፡ እነሱ ቆመው እንዴት ነው ሰው የሚታከመው? ሰው ይኾናልስ ወይ? ልብና ሳንባ መስራት አቁመው የሚሰጠውስ ህክምና ምን ዓይነት ነው? ስንል ጠይቀናቸዋል፡፡ ከተከታዩ ጥንቅር ያንብቡ፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ዶ/ር ፈቀደ እና ባልደረቦቻቸው በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ታሪክ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ተግባርን ፈጽመዋል ይባላልና ምንድነው የከፈታችሁት አዲስ ምዕራፍ? የሰራችሁትስ ምንድን ነው?
ዶ/ር ፈቀደ፡ አዲስ ምዕራፍ ነው የከፈታችሁት የሚለው ትክክል ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የልብና የሳንባን ስራ ተክቶ በሚሰራ ማሽን ልብና ሳንባን በማቆም ልብን ከፍቶ ‘ኦፕሬሽን’ የመስራት ስራ ከተለያዩ የዓለም ሃገራት እየመጡ በተለያዩ ሆስፒታሎች ሲሰሩ ለነበሩ (ሚሽነሪዎች) የተተወ ነው፡፡ በእኛ የልብ ማዕከል ( የኢትዮጵያ ልብ ማዕከል) እንኳን ከ2009 እስከ 2017 የሃገራችን ብዙ ታካሚዎች በሚሽነሪዎች ታክመዋል፡፡ ይሄ የፈረንጅ ድንበር ብቻ ነበር፡፡
ነገር ግን እኔ ከትምህርት ከተመለስኩበት ከ2017 ጀምሮ ከእኔ ከልብ ጠጋኙ፣ የልብና የሳንባን ስራ ተክቶ ከሚሰራው ማሽን ዘዋሪዎች ጀምሮ ሙሉ የልብ ጥገና ቡድን በሃገራችን መሬት በሃገራችን እውቀት ለመጀመሪያ ጊዜ ያለምንም የውጭ ዜጋ ተሳትፎ የመጀመሪያውን ቀዶ ጥገና ሰኔ 5 ቀን 2009 ዓ/ም አድርገናል፡፡ ከዚያም ወዲህ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ብዙ የሃገራችን ሰዎች መድሃኒት ለመሆን ችለናል፡፡ ይህ አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ የአቅርቦት ችግር እስከሌለ ድረስ በአሁኑ ሰዓት ከ95 በመቶ በላይ ግልጋሎቱን ለመስጠት እንችላለን፡፡ ህክምናው ያኔ የህክምና መሳሪያዎቹ ባልነበሩበት በ1970ዎቹ በእነ ፕ/ር አስራት ወልደየስ ሲሞከር ከነበረው የተለየ መደበኛ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ያልተለመደ የልብ ቀዶ ህክምና መንገድን አስተዋውቀዋል በሚል ሲወደሱ እንሰማለንና፡፡ ምንድነው አዲስ ነው የተባለለት ህክምና?
ዶ/ር ፈቀደ፡ አዎ! ልክ ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት ለሃገራችን የመጀመሪያ የሆነውን ‘ቤንታል ፕሮሲጀር’ (ቤንታል ቀዶ ህክምና) ሰርተናል በሃገራችን፡፡
‘ቤንታል ፕሮሲጀር’ በሃገራችን ልጆች፤ በሃገራችን እውቀት የሰራነው ትልቁ ቀዶ ህክምና ነው፡፡ የሚፈራ የቀዶ ህክምና ዓይነትም ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ውስብስብነቱ ነው፡፡ ምናልባትም በልብ ቀዶ ጥገና ረጅም ዓመት የሰሩ አንቱ የተባሉ ፕሮፌሰሮች የሚሰሩት ነው፡፡ 50/60 ልብ ቀዶ ጠጋኝ ባለበት አንድ ወይ ሁለት ሰው ብቻ የሚሞክረው የቀዶ ጥገና ዓይነት እንደሆነም በትምህርት ቤት ቆይታችን ተመልክተናል፡፡
እና ልክ የዛሬ ዓመት እንዳልክ ለተባለ የ23 ዓመት ወጣት 9 ሰዓት የፈጀ የተሳካ ኦፕሬሽን ሰርተን ህይወቱን ታድገናል፡፡ ይሄ በሃገራችንም ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራትም ያለማንም የውጭ ሃኪም ተሳትፎ በራሳችን አቅም የሰራነው አዲስ ታሪክ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ በ4 ዓመታት ውስጥ አደረግሁ ካሏቸው 326 የልብ ቀዶ ጥገናዎች ውስጥ 290 ገደማዎቹ ሙሉ በሙሉ የልብና የሳንባን ስራ በማቆም የተሰሩ ናቸው ብለውናል፡፡ ልብና ሳንባ ቆሞ እንዴት ነው ስራ የሚሰራው? ሰው ይኾናልስ?
ዶ/ር ፈቀደ፡ (ሳቅ) አዎ ሰውማ ይኾናል ዶ/ር ጆን ጊቭ ከ15 ዓመታት በላይ ሲመራመር ቆይቶ በ1953 ይህን ማሽን መስራቱ ለዓለም ሲያበረክት ያውቀው ነበር፡፡ ልብ እየመታ ደም እየፈሰሰ ለመስራት የማይቻለው ይህ ኦፕሬሽን መሰራት ያለበት ልብም ሳንባም ቆሞ ተክቶት የሚሰራ ማሽን ሲኖር ነው በሚል ነው፡፡ ማሽኑን በመስራቱ በርካቶችን ለመታደግ ችሏል፡፡
እና እንደዚህ ዓይነት ኦፕሬሽኖችን ለመስራት ልብም ሳንባም መቆም አለበት፡፡ ልብ ማለት ህይወት ማለት ነው፡፡ሞተር ማለት ነው፡፡ ይህን አቁመህ ነው ማሽኑ ተክቶት እንዲሰራ የምታደርገው፡፡
የልብ ቀዶ ጥገና ሲሰራ ልብና ሳንባ ቆሞ ነው፤ አልፎ አልፎ ልብ እየመታ የምንሰራቸው ኦፕሬሽኖች ቢኖሩም፡፡ ይህ በተለያዩ የህክምና ሂደቶች የሚሰራ ነው፡፡
የመጀመሪያው ሂደት ደረት መክፈት ነው፡፡ 2ኛው የሰውነታችንን የደም ዝውውር ለማሽኑ መስጠት ነው፡፡ 3ኛው ልብና ሳንባን ማቆም ነው፡፡ 4ኛው ልብን ከፍቶ ችግሩን መፍታት እና 5ተኛው ልብና ሳንባን ማስነሳት ነው፡፡ በ6ኛ ደረጃ ደግሞ ልብና ሳንባን ከማሽኑ የማላቀቅ ሂደት (ዊኒንግ ፕሮሰስ) ነው፡፡ በልብ ቀዶ ጥገና ከባዱ ይሄ ነው፡፡ ይሄን በሰላም ከታለፈ ከዛ በኋላ ችግር የማጋጠሙ ነገር እምብዛም ነው፡፡ በመጨረሻ የሚደሙ ነገሮችን በሙሉ አቁሞ አጽድቶ የከፈትነውን መዝጋት ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ከባልደረቦችዎ ጋር በመሆን አቋቁመውታል የሚባልለት ‘ሂሊንግ ቫልቭስ ኢትዮጵያ’ ምንድነው? ለምንስ ተቋቋመ?
ዶ/ር ፈቀደ፡ ይሄ በጣም ትልቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱ እኔ የተሰጠኝና የምኖርበት የማላውቀው እድሜ አለ፡፡ በዚህ እድሜ የምችለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማበርከት እፈልጋለሁ፡፡
ከግለሰብ ይልቅ ሰብሰብ ብለን እንደ ድርጅት ወገኖቻችንን ለምን አናግዝም ብለን በየቀኑ ወረፋ እየጠበቁ የሚሞቱ ወገኖቻችንን በነጻ በሙያችን ለማገልገል ያቋቋምነው ተቋም ነው፡፡
‘ሪሶርስ’ አግኝተን በዓመት እስከ 50 ሰው፤ በሳምንት አንድ ሰው እንኳን ካዳንን በነጻ እንስራ ብለን አስበናል፡፡
ይህን ሃሳብ ይዘን ስንነሳ ሁለት ሶስት ዓመት ሆኖናል፡፡ ግን እንደ ድርጅት የወጣነው መስከረም ላይ ጠቅላላ ጉባዔያችንን አካሂደን ጥቅምት ላይ በበጎ አድራጎት ማህበርነት ተመዝግበን ህዳር ላይ ፈቃዱን ካገኘን በኋላ ነው፡፡ ጤና ጥበቃም ፕሮጄክታችንን ገምግሞ ሚያዚያ ላይ እውቅና ሰጥቶናል፡፡ በሙሉ አቅሙ ሊያግዘን ረጂ አካላትን ሊያስተባብርልንም ቃል ገብቶልናል፡፡
ይህን ካደረግን በኋላ ከግንቦት ወዲህ በግል ጥረት በጓደኞቻችን ትብብር ባሰባሰብነው ሃብት ሁለት ህጻናትን ለማከምና ህይወታቸውን ለመታደግ ችለናል፡፡ አንደኛው ከሻሸመኔ ኮፈሌ ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ የመጣና ዳቢ ተብሎ የሚጠራ የ17 ዓመት ታዳጊ ሲሆን ሁለተኛው ሳማ ሰንበት ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ በሰዎች ጥቆማ የመጣና ቴድሮስ የሚባል የ16 ዓመት ታዳጊ ነው፡፡
ግን እርዳታውን ሳናገኝ ቀርተን ያላከምናቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም አሉና ሊረዱን የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ ብዙ ህጻናት እጃችን ላይ አሉ ሊያግዙን ይችላሉ፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ በስተመጨረሻ በተለይ እንደርስዎ ሊወራ የሚችል የህይወት ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች ያለፉበትን በተለያዩ መንገዶች ያጋራሉና በቀጣይ ከእርስዎ ምን እንጠብቅ?
ዶ/ር ፈቀደ፡ በተቻለን አቅም የሰራናቸውን ነገሮች ከስር ከስር በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ለመጻፍ እንሞክራለን፡፡ አንድ አራቱ ታትመዋል፡፡ ተራ የሚጠባበቁ ሁለት ሶስት ደግሞ አሉ፡፡
በልብ ቀዶ ጥገና ታሪክ ላይ የሰራናቸውን አንኳር ነገሮች ህዝብ እንዲያውቅ ወደፊት በህክምናውም ላይ ያሉ ሰዎች እንዲረዱት፤ ታሪክ እንዳይዛባ ሂደቱን ትውልድ እንዲረዳ ስለምንፈልግም በአማርኛ መጽሃፍ ጽፈናል፡፡ ጽሁፉ አልቆ በአርትኦትና አንዳንድ ስራዎችን በማስተካከል ላይ ነው፡፡ በቅርቡ ታትሞ ለአንባቢያን ይደርሳል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ አመሰግናለሁ፡፡
ዶ/ር ፈቀደ፡ አመሰግናለሁ፡፡