በኢትዮጵያ በልምምድ ላይ የነበረ አውሮፕላን በደረሰው አደጋ የአንድ ታዳጊ ህይወት አለፈ
በኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲ አብራሪነት ስልጠና ላይ የነበሩ ሰልጣኞች አደጋ አድርሰዋል ተብሏል
ሰልጣኞቹ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ነገሌ አካባቢ አውሮፕላኑን ለማሳረፍ ሲሞክሩ አደጋውን እንዳደረሱት ተገልጿል
በኢትዮጵያ በልምምድ ላይ የነበረ አውሮፕላን አንድ ሰው ገደለ፡፡
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርስቲ ባወጣው መግለጫ በተቋሙ ስር ያለው የሐዋሳ ቅርንጫፍ ሰልጣኞች በልምምድ ላይ እያሉ አደጋ እንዳጋጠማቸው ገልጿል፡፡
በመደበኛው የፓይለት ስልጠና ልምምድ ላይ የነበረ ቀላል የተማሪዎች መለማመጃ አውሮፕላን (Dimond DA40NG) አየር ላይ ሳለ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት አርሲ ነጌሌ አካባቢ ለማረፍ ተገድዷል ሲልም አክሏል።
በዚህም ምክንያት በመደበኛ ስልጠናው ላይ የነበሩት አስተማሪውና ተማሪው የመለማመጃ አውሮፕላኑ ሕብረተሰቡ ላይ አደጋ በማያደርስ ሁኔታ ለማሳረፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን የገለጸው ዩንቨርሲቲው ለማረፍ በተደረገው ጥረት መሬት ላይ በነበረች አንዲት ታዳጊ ላይ ጉዳት እንደደረሰ አስታውቋል፡፡
ዩንቨርሲቲው በመግለጫው አክሎም ለተፈጠረው ክስተት ሁሉ ማዘኑን ገልጾ በአደጋው ለተጎዳችው ታዳጊ እና ቤተሰቦቿ መፅናናትን ተመኝቷል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የህይወት ዘመን ሽልማት አበረከቱ
የአደጋው መንስኤ በሚመለከታቸው አካላት በመጣራት ላይ እንደሆነም የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርስቲ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲ የተለያዩ የአቪዬሽን ባለሙያዎች በማሰልጠን የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በአቪዬሽን ቴክኒክ ሙያ፣ የበረራ መስተንግዶ፣ ምግብ ዝግጅት እና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ስልጠናዎችን በመስጠት ለይ ነው፡፡
ዩንቨርሲቲው ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ የውጭ ሀገራትን ሰልጣኞች ተቀብሎ የሚያስተምር ሲሆን ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራትም የአቪዬሽን ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትናንትናው ዕለት አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ዳር ከተሰኘ ኩባንያ ጋር የግንባታ ዲዛይን ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡
በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው አዲሱ የአውሮፕላን ጣቢያ በቢሾፍቱ ከተማ እንደሚገነባ ገልጿል።
ይህ አውሮፕላን ማረፊያ ወይም ኤርፖርት የሚገነባው በዓመት 25 ሚሊዮን መንገደኞችን ብቻ የማስተናገድ ያለው ቦሌ ዓከም አቀፍ ኤርፖርትን ለመተካት እንደሆነ የተቋሙ ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በስምምነቱ ወቅት ተናግረዋል።
በቢሾፍቱ ልዩ ስሙ አቡ ሴራ በተባለው ስፍራ የሚገነባው ይህ ኤርፖርት ግንባታ ዲዛይን መቀመጫውን አረብ ኢምሬትስ ያደረገው ዳር የተሰኘው ኩባንያ መመረጡንም አቶ መስፍን ገልጸዋል።
አቶ መስፍን አክለውም አዲሱ ኤርፖርት ግንባታ በአምስት ዓመታት ውስጥ በሁለት ዙር ይገነባል ያሉ ሲሆን ለመጀመሪያው ዙር ግንባታ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይደርግበታልም ብለዋል።