
ፖሊስ ከሐኪሞች ጋር ባደረገው ምርመራ አልማዞቹ ሆዱ ውስጥ እንዳሉ ተረጋግጧል
770 ሺህ ዶላር የሚያወጡ የአልማዝ ጌጣጌጦችን የዋጠው ሌባ
አሜሪካዊው ጃይታን ላውረንስ የ32 ዓመት ሰው ሲሆን ከሰሞኑ በፍሎሪዳ ውስጥ ባለ አንድ ቅንጡ እና ውድ የጌጣጌጥ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ይገባል፡፡
ከአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር እንደመጣ እና ከኦርላንዶ ማጅክ ክለብ እንደሚጫወት ለጌጣጌጡ መሸጫ ይናገራል፡፡
የቲፋኒ አልማዝ መሸጫ ማዕከልም ግለሰቡን ወደ ቪአይፒ ክፍል ካስገቡት በኋላ የሚፈልገውን ጌጣጌጥ እንዲገዛ ምርጫ ያስቀምጡለታል፡፡
ለስርቆት የገባው ይህ ሰውም ወዲያውኑ ነበር የአልማዝ ጌጣጌጦችን ከተቀመጡበት መስረቅ የጀመረው፡፡ የጌጣጌጥ ሸጮቹ ሁኔታውን ከተጠራጠሩ በኋላ ለፖሊስ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ወዲያውኑ በስፍራው ይደርሳል፡፡
ማለጥ እንደማይችል የተረዳው ይህ ሰውም እያንዳንዳቸው 609 ሺህ ዶላር እና 160 ሺህ ዶላር የሚያወጡ ሁለት የአልማዝ የጆሮ ጌጦችን ውጧቸዋል፡፡
ፖሊስ በስርቆት ወንጀል ጠርጥሮ ያሰረውን ይህን ሌባ ባደረገው ተጨማሪ ምርመራ ማዕድናቱ በሆዱ ውስጥ መቀመጣቸውን አረጋግጧል፡፡
ግለሰቡ ከዚህ በፊትም ውድ ማዕድናት በሚገኙባቸው ሱቆች ላይ የረቀቁ የስርቆት ወንጀሎችን በመፈጸም ልምድ አለው የተባለ ሲሆን ከዚህ በፊት 587 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸው የአልማዝ ማዕድናትን ሰርቆ ነበር ሲል ኤንቢሲ ዘግቧል፡፡
እንዲሁም በኮሎራዶ ግዛት በፈጸማቸው ተደጋጋሚ ወንጀሎች ምክንያት 48 ጊዜ የእስር ማዘዣ ትዕዛዝ ተላልፎበትም ተገኝቷል፡፡
ይሁንና በሌባው ሆድ እቃ ውስጥ የተገኙት አልማዞች በምን መልኩ ለባለቤቱ ሊመለስ እንደታሰበ በዘገባው ላይ አልተጠቀሰም፡፡