ከአንጎላ የአልማዝ ማዕድን ማውጫ በወጣ መርዛማ ፈሳሽ በዴሞክራቲክ ኮንጎ 12 ሰዎች ሞቱ
በመርዛማ ፍሳሹ አማካኝነት 4 ሺህ 500 ሰዎች መታመማቸውም ተነግሯል
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለጉዳቱ ካሳ ያስፈልገኛል ያለች ሲሆን፤ መጠኑን ግን አልተናገረችም
ከአንጎላ የአልማዝ ማዕድን ማውጫ ባመለጠ መርዛማ ፍሳሽ አማካኝነት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የ12 ሰዎች ህይወት መቅጠፉ ተነገረ።
ወደኮንጎ ወንዝ በፈሰሰው መርዛማው ፍሳሽ አማካኝነት ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች በተጨማሪ 4 ሺህ 500 ሰዎች ለህመም መዳረጋቸውም ነው የተነገረው።
ከጎረቤት ሀገር አንጎላ የወጣው መርዛማው ፈሳሽ ወደ የኮንጎ ወንዝ ቀለምን ወደ ቀይነት የቀየረ ሲሆን፤ ወንዙ ውስጥ የነበሩ በርካታ አሳዎች መሞታቸውን እና ሰዎችም አሳዎቹን መመገባቸውን የዴሞክራቲን ሪፐብሊክ ኮንጎ የአካባ ሚኒስቴር ኢቭ ባዛይባ ተናግረዋል።
ዴሞክራቲን ሪፐብሊክ ኮንጎ ለደረሰባት ጉዳት ካሳ ትፈልጋለች ያሉት ሚኒስትሯ፤ መጠኑን ግን ከመናር ተቆጥበዋል።
የአንጎላው የማዕድን አውጪ ካቶካ ስለ መርዛማ ፍሳሹ እስካሁን የሰጠው ምላስ የለም። እንደ ሮይተርስ ዘገባ ካቶካ ማይንስ የአንጎላ 75 በመቶ የአልማዝ ማእድን ምርትን የሚያመርት ተቋም ነው።
ከኩባንያው ማጠራቀሚያ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ መርዛማ የሆነ ፈሳሽ አምልጦ በመውጣቱ የኮንጎ ወንዝን ቀለም ወደ ቀይነት የቀየረ ሲሆን፤ ጉማሬዎችን እና አሳዎችን ጨምሮ በርካታ እንስሳቶችን መግደሉም ተነግሯል።