ቦትስዋና ከአለማቀፉ የአልማዝ ምርት 20 በመቶውን ድርሻ ትይዛለች
ቦትስዋና በአለማችን በግዝፈቱ ሁለተኛ የሆነውን የአልማዝ ማዕድን አገኘች።
ከቦትስዋና መዲና ጋቦሮኒ በ500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ካሮዌ የማዕድን ማውጫ ስፍራ የተገኘው አልማዝ 2492 ካራት ነው ተብሏል።
የማዕድን ማውጫ ስፍራው በካናዳው ሉካራ ዳይመንድ ኩባንያ የሚተዳደር ነው።
ሉካላ ዳይመንድ የተገኘውን አልማዝ የጥራት ደረጃ እና ምን ያህል ሊያወጣ እንደሚችል አለመጥቀሱን ሲቢኤስ ኒውስ አስነብቧል።
የቦትስዋና መንግስት በማራዌ የተገኘው አልማዝ በደቡባዊ አፍሪካ በግዝፈቱ ቀዳሚው ነው ብሏል።
በሀገሪቱ ትልቁ አልማዝ የተገኘው በ2019 ሲሆን 1758 ካራት ነበር።
ከአለማችን የአልማዝ አምራቾች ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሰለፈው ቦትስዋና፥ ከአለማቀፉ የአልማዝ ምርት 20 በመቶውን ድርሻ ትይዛለች።
ይሁን እንጂ የደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር በሚገባ እንደማትጠቀምበት ይነገራል።
የሀገሪቱ መንግስት ባለፈው ወርም የማዕድን ማውጣት ፈቃድ የሚያወጡ የውጭ ኩባንያዎች 24 በመቶ ድርሻቸውን ለሀገሪቱ ዜጎች እንዲሸጡ የሚያስገድድ ህግ ማውጣቱን ሬውተርስ አስታውሷል።
በአለማችን ቀዳሚ ሆኖ የተመዘገበው በደቡብ አፍሪካ በ1905 የተገኘው አልማዝ ነው።
3106 ካራቱ አልማዝ የብሪታንያ የንጉሳውያን ቤተሰቦች ማጌጫ ሆኖ ነበር።
በቦትስዋና ካሮዌ የተገኘ 1 ሺህ 111 ካራት አልማዝ በ2017 በ53 ሚሊየን ዶላር መሸጡን ቢቢሲ ዘግቧል።