ከጦርነቱ ለመሸሽ በሚል ውሻዋን ተሸክማ ፖላንድ የገባችው ዩክሬናዊት ዓለምን እያነጋገረች ነው
በቅጡ መራመድ እንኳን የማይችል የ12 አመት ጀርመናዊ እረኛ አብሯት ሲጓዝ የነበረ መሆኑም ብዙዎችን አስገርሟል
የ37 ዓመቷ አሊሳ “ፖሊያ” የተሰኘ ውሻዋን በትከሻዋ ተሸክማ 17 ኪሎ ሜትሮችን ያህል ተጉዛ ፖላንድ ገብታለች
ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ለመሸሽ በሚል ውሻዋን ተሸክማ 17 ኪሎ ሜትሮችን ያህል የተጓዘችው ዩክሬናዊት እያነጋገረች ነው፡፡
ዩክሬናዊቷ እንስት አሊሳ በጦርነቱ ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገው ህይታቸውን ማትረፍ ከቻሉ ሰዎች እንዷ ናት፡፡
አሊሳ ከሩሲያ ኃይሎች በራሪ ጥይቶች ስታመልጥ ግን ራሷን ብቻ ይዛ አልነበረም፤ የምትወደውንና በእድሜ የገፋውን “ፖሊያ” የተሰኘ ውሻዋን በትከሻዋ ተሸክማ እንጂ፡፡
ይህን በአግራሞት የዘገበው የጣሊያኑ ጋዜጣ ላ-ስታምፓ እጅግ አስገራሚ የሰብዓዊነት ምልክት ሲል ለተደራሲያኑ አስነብቧል፡፡
አሊሳ ድንበር አሳብራ ወደ ፖላንድ ለመዝለቅ ካደረገችው አድካሚ ጉዞ በኋላ፤ ከላ-ስታምፓ ጋር በነበራት ቆይታ "ሁሉንም ነገር አጥተናል፤ አባቴን አጥቻለሁ፤ ባለቤቴ የት እንዳለ አላውቅም ድንበር ሳያቋርጥ ነው የቀረው፤ ውስጤ ክፉኛ አዝኗል በህይወቴ ለአፍታም ተለይቼው ከማላውቀው ባለቤቴ ጋር አሁን አብረን አይደለንም፤ አጠገቤ የለም፤ ሁሉም ወንዶች ከኛ ጋር የሉም" ማለቷም ፤ጦርነቱ በአሊሳና መሰል የሀገሯ ዜጎች ላይ እየፈጠረው ያለው ጠባሳ የበርካቶችን ልብ የሚሰብር የየእለቱ ሁነት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
አሳዛኙ የአሊሳ ታሪክ አሁን ላይ በሰፊው በማህበራዊ ሚድዎች ላይ እየተዘዋወረ ሲሆን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረቱ በዩክሬን ምድር እየተከናወነ ስላለው አስከፊው የጦርነት ትያትር ላይ እንዲያደርግ አስገድዷል፡፡
አሊሳ አድካሚ ጉዞ ስታደርግ “ፖሊያ”ን በጀርባዋ ተሸክማ ነበረ፡፡ በቅጡ መራመድ እንኳን የማይችለው የ12 አመቱ ጀርመናዊ እረኛ አብሯት ሲጓዝ የነበረ መሆኑም የብዙዎችን ልብ ሰብሯል፡፡
ጦርነቱ እየተጋጋለ በመምጣቱ እናቷን፣ እህቷን፣አራት ልጆቿን እና ሁለት ወሾቿን በመያዝ በአንዲት አነስ ያለች መኪና ወደ ፖላንድ ድንበር ጉዞ መጀመራቸውን የምትናገረው የ37 ዓመቷና የኮምፒዩተር ባለሙያዋ አሊሳ፤ ከ16 ሰዓታት ጉዞ በኋላ በፓላንድ ድንበር አቅራቢያ መድረሳቸውን ትናገራለች፡፡
ሆኖም ተሽከርካሪ ባለመገኘቱ 17 ኪሎ ሜትሮችን በእግሯ ለመጓዝ ተገዳለች፡፡ በዚህን ጊዜም እምብዛም ርቀቶችን ለመጓዝ ያልቻለው ውሻዋ አብሯት ነበረ፡፡ ትታው ልትሄድ ያልፈለገችውን “ፖሊያ”ን በጀርባዋ ተሸክማም ፖላንድ ገብታለች፡፡