ስብሰባው ሩሲያ፤ አሜሪካ በዩክሬን የስነ ህይወታዊ ጦር መሳሪያዎችን ታንቀሳቅሳለች ስትል በመክሰሷ የሚካሄድ ነው
ሩሲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ስብሰባ እንዲያደርግ መጠየቋን በድርጅቱ የሀገሪቱ ምክትል መልዕክተኛ አስታወቁ፡፡
ሞስኮ ስብሰባው እንዲጠራ የፈለገችው በአሜሪካ እንደሚደገፍ በገመተችውና በዩክሬን አለ በተባለው የስ ህይወታዊ ጦር መሳሪያ (ባየሎጂካል ዊፐን) ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተመድ የሩሲያ ምክትል መልዕክተኛ ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ ስብሰባው እንዲደረግ ጥያቄ መቅረቡን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ የተመድ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሩሲያ፤ አሜሪካ በዩክሬን የባይሎጂካል ጦር መሳሪያ ቤተ ሙከራዎችን ስራ ላይ እያዋለች መሆኑን አስመልክቶ ጥያቄዎችን ብታነሳም ውሸት ነው የሚሉ ምላሾች እየተሰጣት ነው፡፡
ዋሽንግተን፤ ሞስኮ ያነሳችውን ጉዳይ አስተባብላ “መሰረት ቢስ” እንደሆነ ገልጻለች፡፡ አሜሪካ፤ ሩሲያ ምናልባትም በዩክሬን የኬሚካል ወይም የባዮሎጂካ ጦር መሳሪያዎችን ልትጠቀም እንደምትችል አስጠንቅቃለች፡፡
ሩሲያ በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል አሜሪካ በዩክሬን ባይሎጂካል የጦር መሳሪያ ቤተ ሙከራ እንዳላት ከገለጸች ከሰዓታት በኋላ ነው አሜሪካ ምላሽ የሰጠችው፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በሀገራቸው የባዮሎጂካ ቤተ ሙከራዎች ወታደራዊ ሳይሆን ለንጹሃንን የሚሆን ሳይንስ ነው ብለዋል፡፡
የኬሚካል ጦር መሳሪያ ወይም ሌላ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ በሀገራቸው እየተሰራ አለመሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
እነዚህን ጉዳዮች በመመልከት ብቻ ዩክሬን የአሜሪካ እና የሩሲያ መሻኮቻ እንደሆነች ማየት ይቻላል እየተባለ ነው፡፡