ሩሲያ፤ ኪቭን ለመክበብ የሚያስችል ግዙፍ ወታደራዊ ኮንቮይ በማንቀሳቀስ ላይ መሆኗ ተገለጸ
የሩሲያን የወታደራዊ ኮንቮይ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እየወጡ ነው
እንቅስቃሴው የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ መጠጋታቸውን የሚያሳይ ነው ተብሏል
ሩሲያ፤ ኪቭን ለመክበብ የሚያስችል ግዙፍ ወታደራዊ ኮንቮይ በማንቀሳቀስ ላይ መሆኗ ተገለጸ፡፡
በእንቅስቃሴው የዬክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ዳግም በሩሲያ ወታደሮች ከበባ ስር ልትወድቅ ትችላለች ተብሏል፡፡
60 ያህል ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን አንድ ግዙፍ የሩሲያ ወታደራዊ ኮንቮይ ወደ ዩክሬኗ መዲና ኪቭ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ወታደራዊ የሳታላይት ምስሎች አመልክተዋል፡፡
ኮንቮዩ ወደ በቀላሉ ወደ ከተማዋ ለመግባት የሚችል ከሆነ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪን ጨምሮ ሌሎች የሃገሪቱ በለስልጣን አለን የሚሉባት ኪቭ ሙሉ በሙሉ በሩሲያ ኃይሎች እጅ የምትወድቅ ይሆናል፡፡
የሩሲያ ወታደሮች በተለያዩ አቅጣጫዎች ማጥቃት መጀመራቸውም ነው የተነገረው፡፡ ሊሰነዘር የሚችልባቸውን የትኛውንም ዐይነት ጥቃት ለመከላከል ይችሉ ዘንድ በስብጥር መሰማራታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
የሚሳኤል ማስወንጨፊያዎች በቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ እንዲቀመጡ መደረጋቸውን የሚያሳዩት ምስሎቹ ኪቭ ደም አፋሳሽ ጦርነትን ልታስተናግድ የመጨረሻው ሰዓት ላይ ለመድረሷ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው ተብሏል፡፡
የሩሲያ የእግረኛ ጦር አባላት ከኪቭ በ25 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ እንደሚገኙም የብሪታኒያ የደህንነት መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
ከሳምንት በፊት ተመሳሳይ የወታደራዊ ኮንቮይ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ምስሎች ይፋ ሆነው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህ በአዲስ መልክ የተነቃቃ የሚመስለው የሩሲያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ያለ ስኬት ከተጠናቀቀው የአንታልያው ውይይት በኋላ የሆነ ነው፡፡
በቱርክ አንታልያ ከተማ የተገናኙት የሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተኩስ ለማቆም ከሚያስችል ስምምነት መድረስ ሳይችሉ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡