በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ጦርነቱ እንዲቆም አድርጓል
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ በህወሃት ሀይሎች መጠቃቱን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው፡፡
- የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በምን ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደረሱ?
- ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በመንግስትና በህወሓት መካከል ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ምን አሉʔ
ይህ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ህይወት ሲቀጥፍ ዜጎችን ለስደት፣ ሰብዓዊ ስደት እና አካል ጉዳት መዳረጉን የተለያዩ የሰብዓዊ ጥበቃ ተቋማት ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በፌደራል መንግስት እና በህወሃት መካከል የተካሄደው ይህ ጦርነት ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ጦርነቱ ቆሟል፡፡
አልዐይን አማርኛ ይህ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ስድስት ወራት ያስቆጠረ ሲሆን የእስካሁኑ የሰላም ስምምነት አተገባበር ምን ይመስላል? በሰሜን ኢትዮጵያስ ዳግም ጦርነት ይነሳ ይሆን? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የሰላምና ፖለቲካ ምሁራንን አነጋግረናል፡፡
ዶክተር ፋና ገብረ ሰንበት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት መምህር ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከሆነ በፌደራል መንግስት እና ህወሃት መካከል በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው ስምምነት ግጭት ወይም ጦርነት የማቆም ስምምነት እንጂ የሰላም ስምምነት ልንለው አንችልም ብለዋል፡፡
ይሁንና ጦርነት ለሰለቸው ህዝብ ይህ ስምምነት ብዙ ትርጉም አለው የሚሉት ዶክተር ፋና ስምምነቱ በተፈረመ ሰሞን የተወሰኑ የተቃርኖ ሀሳቦች ቢነሱም ቀስ በቀስ ግን ህዝቡ ስምምነቱን እንደተቀበለው አክለዋል፡፡
ጦርነቱ መቆሙ፣ በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ አገልግሎቶች ቀስ በቀስ መጀመራቸው፣ የሕዝብ መተማመንን የሚያዳብሩ ስራዎች ቀስ በቀስ እየተጀመሩ መሆናቸው የስምምነቱ ውጤቶች መሆናቸውንም ዶክተር ፋና ጠቅሰዋል፡፡
በጦርነቱ ለደረሱ ጉዳቶች ተጠያቂነት፣ የፖለቲካ ልዩነቶች፣ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች ጉዳይ እና ሌሎችም እስካሁን በደቡብ አፍሪካው ስምምነት መሰረት እስካሁን ያልተሰሩ ስራዎች እንደሆኑ የሰላምና ደህንነት መምህሩ ተናግረዋል፡፡
ለጦርነቱ መጀመር ምክንያት ናቸው በሚል ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረቶች ገና አለመጀመራቸው ዋነኛ ስጋት እንደሆኑ የሚናገሩት ዶክተር ፋና ፖለቲከኞች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ማህበረሰብ ሲወያዩባቸው ሊፈቷቸው የሚችሉ ናቸውም ብለዋል፡፡
ያልተፈቱ የሚባሉት የልዩነት ጉዳዮች በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት እንዲጀመር ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም “ለልዩነት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ብዙ እና ረጅም ጊዜ የፈጁ ቢሆንም በውይይቶች መፈታት የሚችሉ ናቸው፣ እዚህም እዛም ኩርፊያ፣ ቅያሜዎች እና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ ቢችሉም ወደ ይፋዊ ጦርነት ሊወስድ የሚችሉ ግን አይደሉም“ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“ጦርነትን የሚደግፉ ፖለቲከኞች ቁጥር ጥቂት ነው፣ ትግራይ ዳግም ወደ ጦርነት ልትገባ የምትችልበት እድል ዝቅተኛ ነው“ የሚሉት ዶክተር ፋና “ህወሃት ከዚህ በፊት ጦርነቱን በጀመረበት መጠን እና ስሌት በአማራ ክልል ተመሳሳይ ጦርነት መጀመር የሚያስችል የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሁኔታዎች ይኖራሉ ብዬም አላስብም” ሲሉ ነግረውናል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው ስምምነትን ቃል በቃል እንዲተገበር መጠበቅ የለብንም የሚሉት ዶክተር ፋና በጦርነት ውስጥ የቆዩት ህዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚያጎለብቱ ስራዎች መሰራት እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል፡፡
ለደረሱ ጥፋቶች እውቅና መስጠት፣ መተማመንን መፍጠር፣ የእርቅ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማጎልበት በቀጣይ መሰራት ያለባቸው ስራዎች እንደሆኑ ዶክተር ፋና አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በየጊዜው ብዙ ክስተቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል፤ ነገር ግን በደሎችን ይቅር ብሎ የሚኖር ማህበረሰብ በመሆኑ የጦርነቱ ጠባሳዎችን የሚረሳበት እና ቀስ በቀስ ወደ አብሮነቱ መግባቱ አይቀርምም ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ የተደረገው የሰላም ስምምነት ከመጀመሪያው ጀምሮ አሳታፊ እና የውጭ ጫናዎች የነበሩበት ነበር የሚሉት ደግሞ በጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሰለሞን ጓዴ ናቸው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ የሰላም ስምምነቱ በዋናነት በጦርነቱ ለደረሱ ጉዳቶች ተጠያቂነት እንዳይኖር ማድረግ፣ በጦር ሜዳ የተደረጉ ሽንፈቶችን መሸፈን ያስቻለ እንጂ ህዝቡ እንደጠበቀው ጦርነቱን በዘላቂነት ሊያስቆም የሚችል አይደለም፡፡
ጦርነቱ ከተካሄደባቸው ክልሎች በተለይም አማራ እና አፋር ክልሎች በሰላም ስምምነቱ ላይ በሚገባ አልተወከሉም የሚሉት መምህር ሰለሞን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከህወሃት ጋር የሚደረገውን ድርድር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ይመራሉ ቢባልም አንድም ጊዜ በድርድሩ ላይ ሲሳተፉ እንዳልታዩም ጠቅሰዋል፡፡
“የሰላም ስምምነት አተገባበሩ አማራ እና አፋር ክልሎችን ስጋት ውስጥ ከቷል” የሚሉት መምህር ሰለሞን በጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ስም የጦርነቱን ዋነኛ የፕሮፓጋንዳ ሰው መሪ አድርጎ ማምጣት ትክክል አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡
በቀጣይ የፌደራል መንግስት እና ህወሃት የይስሙላ ተጠያቂነትን አስፍነናል ለማለት ዋነኛ ጥሰት ፈጻሚዎችን ሳይሆን ተራ አዋጊዎችን ሊያስሩ እንደሚችሉም መምህር ሰለሞን ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
መምህር ሰለሞን አክለውም በአማራ ክልል የሚነሱ የይገባኛል መሬቶች ጥያቄ ምላሽ አለመሰጠት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥያቄዎችን ለመፍታት ፍላጎት አለመኖር፣ የትግራይ ፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች የጦርነት ጉሰማ መቀጠላቸው ሲታይ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት የመቀስቀስ እድሉ ሰፊ ነው ብለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የኤርትራ ጦር ዳግም ወደ ኢትዮጵያ የመግባት እድሉ ሰፊ ይሆናል የሚሉት መምህር ሰለሞን የፌደራል መንግስትም ከቀውሶች ለማትረፍ ከሚሰራ ይለቅ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ፍለጋዎች ላይ እንዲያተኩር መምህር ሰለሞን ይመክራሉ፡፡
በሰላም ስምምነቱ መሰረት የሕወሃት ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ የሚያደርጉ ስራዎችን በስፋት መስራቱ እንዳለ ሆኖ ይህ ጉዳይ በአማራ እና አፋር ክልል ያሉ መደበኛ ያልሆኑ ታጣቂዎችንም ማካተት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በጦርነቱ የወደሙ የግል እና የመንግስት ተቋማትን ዳግም ወደ ገልግሎት ለማስገባት በወጥነት በሶስቱም ክልሎች መሰራት ያለበት ቢሆንም የፌዳራል መንግስት እና ሌሎች ተቋማት ትኩረታቸውን ሁሉ ትግራይ ክልል ማድረጋቸው ስህተት እንደሆነም መምህር ሰለሞን ጠቅሰዋል፡፡