ሁለቱ ወገኖች መቸ ስምምነት ያደርጋሉ ለሚለው ጊዜ ማስቀመጥ እንደማይቻል አንስተዋል
በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ከህወሃት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የቡድኑ ቃል አቀባይ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ወገኖች በትግራይ ክልል መቀሌ “በቀጠናዊ ጉዳዮች” ላይ መምከራቸውንም የገለጹት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብር የተፈረጀው ህወሃት ቃል ጌታቸው ረዳ ናቸው።
ቃል አቀባዩ፤ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እና ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በ ``ቀጣናዊ ጉዳዮች” ላይ እንደተወያዩ ይግለጹ እንጅ ቀጠናዊ የተባሉት ጉዳዮች ምን እንደሆኑ በግልጽ አላስቀመጡም ነበር።
በአፍሪካ ቀንድ የሕብረቱ ከፍተኛ ተወካይ እንዲሁም የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ በመቀሌ ያረጉትን ጉዞ በተመለከተ ከቢቢሲ አፍሪካ የራዲዮ ፕሮግራም ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ከፍተኛ ተወካዩ የአፍሪካ ሕብረት በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በተመለከተ ትኩረት ሰጥቶታል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ፤ ሕብረቱ እርሳቸው በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን እንዲያጎለብቱ መሾሙ ጉዳዩን በደንብ እንደያዘው እንደሚያመለክት ገልጸዋል።
በፌደራል መንግስቱ እና በህወሃት መካከል ሰላም እንዲፈጠር በዝግታም ነገር ግን ያልተቋረጠ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ለሰብአዊነት ሲባል የተደረገው የተኩስ አቁም እንዳለ ያነሱት ኦባሳንጆ፤ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ ከስድስት ወራት በፊት ከነበረው ሁናቴ የተሻለ እንደሆነም ገልጸዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን እንዲመጣና ወደ ንግግር እዲያመሩ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን ነው የአፍሪካ ቀንድ ተወካዩ ለቢቢሲ የተናገሩት።
አሁን እየተደረገ ያለው ጥረት ሁለቱ ወገኖች ወደ ተኩስ አቁም እንዲመጡ ማድረግ እንደሆነ ያነሱት ተወካዩ በትግራይ ክልል ቆይታቸው ዩኒቨርሲቲ መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
የሕብረቱ የመጨረሻ ግብ መደበኛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ መሆኑን ያነሱት ኦባሳንጆ፤ መቼ የሰላም ስምምነት ሊፈራረሙ እንደሚችሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ እንደሚያስቸግር ገልጸዋል። ነገር ግን መግባባት እንዲፈጠር ስራችንን እንቀጥላለን ሲሉም ነው የተናገሩት።
ድርድርን በተመለከተ ቁርጥ ያለ ቀን አልተቀመጠም ያሉት ኦባሳንጆ ሶስት፣ ስድስት ወር ወይም ዓመት ይሁን አይታወቅም ብለዋል።
በትግራይ የተቋረጡ እንደ የመብራት፣ የውሃ እና የባንክ አገልግሎቶችን የመሳሰሉ የመሰረተ ልማቶች ዳግም አገልግሎት መስጠት እንደጀምሩም ንግግር መደረጉን ተወካዩ አንስተዋል።