በሀገራችን ንጹህ ኃይል ለመደገፍ ሱልጣን አል ጃብር ላበረከቱት ሚና እናመሰግናለን- ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ
አረብ ኤምሬትስ የኮፕ 28 ጉባኤውን ማዘጋጀቷ ወደ ተጨባጭ መፍትሄዎች ይመራሉ ብለዋል
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ኢትዮጽያ የአየር ንብረት ቀውስን በመጋፈጥ "ግንባር ቀደም" ከሚባሉት ሀገራት መሀል ናት አሉ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኮፕ 28 ጉባኤ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃብርን ተሞክሮዎች አድንቀው በጉባኤው ዝግጅት ላይ ያላቸውን እምነት አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጉባኤውን ማዘጋጀቷ ወደ ተጨባጭ መፍትሄዎች ይመራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ሱልጣን አል ጃብር የመስዳር ኩባንያ ፕሬዝዳንት ሆነው በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን በመደገፍ እና የሀገሪቱን ንጹህ ኤሌክትሪክ የማምረት አቅምን በማስፋፋት ላበረከቱት ሚና በትዊተር ገፃቸው አመስግነዋል።
የአየር ንብረት ቀውስን በመጋፈጥ "ግንባር ቀደም" ከሚባሉት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ዐቢይ አህመድ አስረድተዋል።
ከፍተኛ የአየር ጸባይ እና ድርቅ የሀገሪቱን ዜጎች እና ሀገራዊ ልማትን በቀጥታ አደጋ ላይ የሚጥለው ከፍተኛ የምግብ እና የውሃ እጦት መኖሩንም ጠቅሰዋል።
"እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ በደቡብ ሀገራት ያለውን የአየር ንብረት ፋይናንስ ክፍተት በማስተካከል በኪሳራና ጉዳት ፈንድ እና የፋይናንስ ዝግጅት ላይ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 27) ውጤት መሰረት ተጨባጭ መሻሻል ማድረግ አለብን" ሲሉም አክለዋል።
በአረብ ኤምሬትስ የኮፕ 28 አዘጋጅነት ኢትዮጽያ ሙሉ እምነት እንዳላት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ጉባኤው በሀገራት መካከል መግባባት መፍጠር የሚችል እና እያንዳንዱን ሀገር፣ ክልል እና የህብረተሰብ ክፍል በማስተባበር ተጨባጭ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን እና ትርጉም ያለው ውጤቶችን ለማቅረብ እንደምትችል በትዊተር ገጻቸው አመልክተዋል።
ዶ/ር ሱልጣን አል ጃብር በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ፣ በመንግስት አስተዳደር እና በንግዱ ዘርፍ ባካበቷቸው ዘርፈ-ብዙ ተሞክሮዎች የዓለም አቀፍ የገንዘብ መሰረተ ልማትን ማሻሻል እና ቀጣይነት ያለው ዝቅተኛ የካርቦን ኢኮኖሚ ልማት ዕድሎችን ለማደስ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።