የአትላንቲክ ካውንስል ፕሬዝዳንት ሱልጣን አል-ጃብር የኮፕ -28 ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸው እንደሚደግፉ ገለጹ
ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪዎችን የሚሳተፉበት የአትላንቲክ ካውንስል ግሎባል ኢነርጂ ፎረም በአቡ ዳቢ እየተካሄደ ነው
ኬምፔ፤ ሱልጣን አል-ጃብር የአየር ንብረት ግቦችን ለማሳካት እውነተኛውን መንገድ ማሳየት የሚችሉ መሪ ናቸው ብለዋል
የአትላንቲክ ካውንስል ፕሬዝዳንት ፍሬድሪክ ኬምፔ ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃቢር (ዶ/ር) የኮፕ-28 ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው እንደሚደግፉ ገለጹ፡፡
ፍሬድሪክ ኬምፔ ሱልጣን አል-ጃብር የአየር ንብረት ግቦችን ለማሳካት እውነተኛውን መንገድ ያሳያሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከአትላንቲክ ካውንስል ግሎባል ኢነርጂ ፎረም ጎን ለጎን በሰጡት አስተያየት ጉባኤውን ለመምራት ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የኢንዱስትሪ እና የላቀ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሱልጣን አህመድ አል ጃብር የተሻለ አማራጭ አለ ብየ አልገምትምም ብለዋል፡፡
“ አንዳንድ የአየር ንብረት ተሟጋቾች በሱልጣን አህመድ አል ጃብር መመረጥ ዙሪያ የሰነዘሩትን ትችት አንብቤያለሁ ነገር ግን እነዚህ አካላት በዓለም ላይ ያለንበትን ሁኔታ በትክክል የተረዱት አይመስለኝም” ሲሉም አክለዋል።
ኬምፔ እንዳሉት የአየር ንብረት ተሟጋቾች ከተፈጥሮአዊ ጋዝ ወይም ነዳጅ ውጭ የኃይል ሽግግር አለመኖሩን መቀበል አለባቸው።
የልቀት መጠንን ለመቀነስ ፈጣኑ መንገድ የድንጋይ ከሰልን ማስወገድ እና የተፈጥሮ ጋዝን መጠቀም ቢሆንም የአየር ንብረት ተሟጋቾች ተፈጥሮአዊ ነዳጅ አልፎ ተርፎም ከኒውክሌር ኢነርጂ ውጭ ማንኛውንም አማራጭ መቀበል ለምደዋል ሲሉም አብራርተዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ንግግራቸው ሲቀጥሉ "የሁለቱ ጉዳዮች ጥምረት አወንታዊ ተግባራዊነትን እንደሚያንጸባርቅ አምናለሁ ... እናም ሱልጣን አል-ጃብር ይህንን ጥበብ የተሞላበት ተግባራዊነት እና የፓሪስ የአየር ንብረት ግቦችን ለማሳካት የሚያስችል ተጨባጭ መንገድን ያሳያሉ ብየ አምናለሁ" ብለዋል፡፡
ኬምፔ ወደ ታዳሽ ኃይሎች የሚደረገውን ሽግግር ለማሳካት ርምጃቸውን በማፋጠን ረገድ የአየር ንብረትን በተጨባጭ ለመቋቋም እንዲችሉ የተፈጥሮአዊ ጋዝ ወይም ነዳጅ አቅራቢዎች ተመሳሳይ መንገድ መከተል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ይህን ማድረግ የጀመሩ እንደ ሼል፣ኤክሶን እና ኢኒ የመሳሰሉ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ በማድረግ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች መኖራቸውን እንደ አብነት በማንሳት፡፡
የአትላንቲክ ካውንስል ግሎባል ኢነርጂ ፎረም የአቡ ዳቢ ዘላቂነት ሳምንት ( Abu Dhabi Sustainability Week) አካል ሆኖ በየዓመቱ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡
ፎረሙ በኢነርጂ ስርዓቱ ውስጥ ያለውን የረጅም ጊዜ ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎችን ለማጥናት በኃይል እና በውጭ ፖሊሲ መስክ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪዎችን የሚሳተፉበትም ነው፡፡
በርካታ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት ይህ ፎረም የተዘጋጀው በተባበሩት አረብ ኢነርጂ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ በአቡ ዳቢ ናሽናል ኦይል ኩባንያ "ADNOC" እና ሙባዳላ ኢንቨስትመንት ኩባንያ ትብብር አማካኝነት ነው ተብሏል፡፡