ግብፃዊው የአረብ ሊግ ዋና ጸኃፊ አቡል ጌት በሕዳሴ ግድብ ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገለጹ
ሱዳንን ለጦርነት የሚገፋፋ ሌላ አካል መኖሩን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ ይታወቃል
የኢትዮጵያ እና የሱዳን የድንበር ውዝግብ "የሱዳንን ሙሉ ሉዓላዊነት በሚያስጠብቅ መልኩ" ሊፈታ እንደሚገባም ገልጸዋል
የአረብ ሊግ ዋና ፀኃፊ አቡል ጌት በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር ከ“አንድ ወገን እርምጃ” በተለየ መልኩ ወደ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ስምምነት ያመራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ግብፃዊው አሕመድ አቡል ጌት ይህን መግለጫ የሰጡት የአረብ ሊግ እና የአፍሪካ ሕብረት ዘጠነኛው የትብብር መድረክ ፣ የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በተገኙበት ፣ ዛሬ ሰኞ በካይሮ በሚገኘው የአረብ ሊግ ዋና መስሪያ ቤት በተካሔደበት ወቅት ነው፡፡
አቡል ጌት “የግድቡ ድርድሮች ወደ ተፈለገው ግብ ያደርሳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ፤ ይህም የሁሉንም ፍላጎት ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ሕጋዊ ፣ አስገዳጅ እና ፍትሃዊ ስምምነት ላይ መድረስ እንዲሁም በግድቡ ሙሌትና የአሠራር ሂደት ላይ መስማማት" ነው ያሉ ሲሆን “ስምምነቱ የግብፅ እና የሱዳንን የውሃ መብት በሚያስጠብቅ መልኩ እንደሚደረስ ተስፋ አለኝ" ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ፣ ግብፅ እና ሱዳን በሕዳሴ ግድቡ ላይ አድካሚ ድርድር ሲያካሂዱ የቆዩ ሲሆን ካይሮ እና ካርቱም በግድቡ የውሀ ሙሌት እና አለቃቀቅ ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ ይፈልጋሉ፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ አስገዳጅ ስምምነት ላይ የመድረስ ፍላጎት የላትም፡፡
ኢትዮጵያ እና ሱዳን የገቡበትን የድንበር ውዝግብ በተመለከተ ፣ ሁለቱ ሀገራት ወደ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው የገለጹት አቡል ጌት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት ብለዋል፡፡
ይሁንና ለሱዳን ወገንተኝነታቸውን በሚያሳይ መልኩ “በመሬቷ ላይ የሱዳንን ሙሉ ሉዓላዊነት በሚያስጠብቅ ሁኔታ እና ይዞታዋን የማስተዳደር ሕጋዊ መብቷን በሚያስጠብቅ መልኩ ነው ስምምነት መደረስ ያለበት” ብለዋል፡፡
ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ወረራ መፈጸሟ በሁለቱ ሀገራት መካከል አሁን ለተፈጠረው ውጥረት መንስኤ መሆኑን በተደጋጋሚ የገለጸችው ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን ወደ ጦርነት እንድትገባ ከኋላ የሚገፋፋትአካል እንዳለ ብታስታውቅም ይህ አካል ማን እንደሆነ ግን በግልጽ ይፋ አላደረገችም፡፡