ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ከዲአር ኮንጎ ፕሬዝደንት ጋር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያዩ
የግድቡ ድርደር ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኮንጎ የመዛወሩን ጉዳይ ግብፅ አጥብቃ እንደምትፈልገው ይነገራል
ኢትዮጵያ በኪንሻሳ ኤምባሲዋን ልትከፍት መዘጋጀቷ ተገልጿል
ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ከፕሬዝደንት ፌሊክስ ቺሲኬዲ ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በዉይይታቸዉም በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየዉን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡ በዚህ ዉይይት ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ የኢትዮጵያን ኤምባሲ በኪንሻሳ መልሶ ለመክፈት መወሰኑን አስታዉቀዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1962 ተከፍቶ የነበረዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እ.ኤ.አ. በ 1980ዎቹ መጀመሪያ በበጀት እጥረት ምክኒያት ተዘግቶ እንደነበረ ይታወሳል፡፡
ሁለቱ ሀገሮች በአቪዬሽን ዘርፍ ስምምነት ያላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወደ ኪንሻሳ፣ ሉቡምባሺና ጎማ ከተሞች ይበራል፡፡
ፕሬዝደንት ቺሲኬዲ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርነትን በመጪው ሳምንት ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት እንደሚረከቡ ይታወቃል፡፡
ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ መሰረት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይትን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአደራዳሪነት እንደምትረከብም ይጠበቃል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ከሀገሪቱ ፕሬዝደንት ቺሴኬዲ ጋር የመከሩት ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ፣ የተጀመረውን የድርድር ሂደት በተሳካ መልኩ እንደሚያስቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ግብፅ እና ሱዳን የአደራዳሪነቱን ሚና ኮንጎ እስክትረከብ ድረስ የድርድሩ ሂደት እንዲዘገይ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህም ድርድሩን አሰልቺ እንዳደረገው የገለጹት ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሁለቱ ሀገራት ወጣ ገባ ሲሉ እና የተለያየ አቋም ሲያንጸባርቁ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ባደረገ ወጥ አቋም መቀጠሏን ተናግረዋል፡፡
የዲአር ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፍሊክስ ቺሲኬዲ ከሳምንታት በፊት ለግብፅ አቻቸው በአማካሪያቸው በኩል በላኩት መልዕክት በሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ሀገራቸው “ከግብጽ ጎን እንደምትቆም” ማረጋገጣቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ካላቸው ቅርርብ የተነሳ ፣ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚደረገው ድርደር ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኮንጎ የመዛወሩን ጉዳይ ግብፅ አጥብቃ ትፈልገዋለች ነው የሚባለው፡፡
ከሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ በተጨማሪ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ አሁን እየተሰራ ስላለው የመልሶ ማቋቋምና የሰብዓዊ እርዳታ ገለጻ ማድረጋቸውን ከኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡