ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ “በውስጥም ሆነ በድንበር ያሉ ጉዳዮች በትኩረት ክትትል እየተደረገባቸው ነው” ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ
የግድቡ ግንባታ በታቀደለት ጊዜና በሚፈለገው መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ትናንት አስታውቀዋል
ለግድቡ ግብዓቶችን በማንኛውም ጊዜ ማድረስ የሚያስችል አስተማማኝ የጸጥታ አደረጃጀት መኖሩን ሌ/ጄ አስራት ገልጸዋል
በመተከል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስጋት እንደማይሆን የዞኑ የተቀናጀ ግብረ-ሃይል አስታወቀ።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማንኛውም ጊዜ ማድረስ የሚያስችል አስተማማኝ የጸጥታ አደረጃጀት እንዳለም ግብረ-ሃይሉ አረጋግጧል።
የመተከልን የተቀናጀ ግብረ ሃይል የሚመሩት ሌተናንት ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እና ሌሎች የግብረ ሃይሉ አባላት የሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።
ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ለኢዜአ እንዳሉት ፣ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ጀምሮ ጸጥታውን ታሳቢ ያደረገ የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላት አደረጃጀት ተፈጥሯል።
“በውስጥም ሆነ በድንበር ያሉ ጉዳዮች በትኩረት ክትትል እየተደረገባቸው በመሆኑ ስጋት አይኖርም” ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከግድቡ ሰራተኞችና አመራሮች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ሌተናንት ጄኔራል አስራት ዴኔሮ “ሃላፊነት በጎደላቸው ማህበራዊ ድረ- ገፆች የሚተላለፉት የተሳሳቱ መረጃዎች የመተከልን ነባራዊ ሁኔታ አይገልጹም” ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ግብዓት በማንኛውም ሰዓት ለማቅረብ ያለጸጥታ ስጋረት የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል።
“የደህንነት ስጋት አለብን” የሚሉ ተሽከርካሪዎችን ማጀብ ደግሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ የተለመደ ስራው መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ በታቀደለት ጊዜና በሚፈለገው መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ትናንት ገልጸዋል፡፡
ሚንስትሩ እና የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ ቦርድ አባላት በትናንትናው ዕለት በስፍራው በመገኘት ግምገማ ካደረጉ በኋላ ነበር የግድቡ ግንባታ በታቀደለት ጊዜ እየተከናወነ እንደሆነና የግንባታ ሂደቱም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ሚንስትሩና የቦርድ አባላቱ የግንባታ ስራውን ከሚያከናውኑ ኮንትራክተሮች ፣ ከባለሙያዎችና አማካሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
ለግድቡ መጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያውያን ከሃገር ውስጥና ውጪ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ከምን ግዜውም በላይ ተጠናክሮ ቀጥሏልም ነው ያሉት።