“በአፍሪካ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኮሮና ታማሚዎች ምልክቶችን አያሳዩም”-የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር
ምልክቱን ሳያሳዩ በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መብዛቱን የቅድመ ጥናት መረጃዎች አመልክተዋል
ሰውነታቸው ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችል ጸረ እንግዳ አካል አዳብሮ እንደሆነ ለማወቅ ጥናቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል
“በአፍሪካ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኮሮና ታማሚዎች ምልክቶችን አያሳዩም”-የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር
አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሊደርስባት ከሚችለው አስከፊ ጉዳት አምልጣ እንደሆነ የሚገመግም የኦንላይን ውይይት ትናንት ተካሂዷል፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች በዚህ ውይይት የተሳተፉት የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማሺድሶ ሞኤቲ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዬን በላይ ሰዎች በቫይረሱ በተያዙባት አፍሪካ ከ34 ሺ የሚልቁ ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል፡፡
ወረርሽኙ በወርሃ የካቲት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አህጉሪቱ ከመግባቱ አስቀድሞ ምላሽ የመስጠት አቅምን ለማሳደግ ሰፊ ዝግጅቶች በመንግስታት ሲደረጉ ነበር ብለዋል፡፡
ከወርሃ መጋቢት ጀምሮ የተወሰዱ እንቅስቃሴንና መሰባሰቦችን የመገደብ እርምጃዎች በቫይረሱ ሊያዙ የሚችሉ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ አስችሏልም ነው ዳይሬክተሯ የሚሉት፡፡
አፍሪካውያን በሰውነታቸው ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችል ጸረ እንግዳ አካል አዳብረው እንደሆነ ለማወቅ ጥናቶች በመካሄድ ላይ ናቸው እንደ ዶ/ር ማሺድሶ ማብራሪያ፡፡
ይህ ማለት ምልክቱን ሳያሳዩ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ብዙ ናቸው ማለት ነው፡፡ የቅድመ ጥናት መረጃዎች ይህንኑ ማመልከታቸውንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
የቅድመ መረጃ ትንተናዎቻችን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአህጉሪቱ የቫይረሱ ታማሚዎች ምልክቶቹን እንደማያሳዩ ይጠቁማሉ ልክ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደታየው ሁሉ የጤና ተቋማቶቻችን በጽኑ የቫይረሱ ታማሚዎች ያልተጨናነቁትም ለዚህ ነው ሲሉም ነው ዳይሬክተሯ የሚያስቀምጡት፡፡
ሆኖም ይህ በወረርሽኙ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን አልቀነሰውም ምንም እንኳን ቁጥሩ በአንጻራዊነት የተሻለ ነው ሊባል ቢችልም፡፡
በመሆኑም ሃገራት የጀመሯቸውን ወረርሽኙን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዶ/ር ማሺድሶ ጠይቀዋል፡፡