ትራምፕ በምርጫ ከተሸነፉ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ ፈቃደኛ አይደሉም ተባለ
ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ታሪክ አንድ ምርጫ ብቻ ጥያቄ ተነስቶበት በፍርድ ቤት ዕልባት አግኝቷል
ፕሬዝዳንቱ በቀጣዩ ምርጫ ከተሸነፉ ሥልጣን ስለማስረከባቸው ተጠይቀው “የሚፈጠረውን እናያለን” ብለዋል
ትራምፕ በምርጫ ከተሸነፉ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ ፈቃደኛ አይደሉም ተባለ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. በቀጣዩ ህዳር 3 በሚካሔደው ምርጫ በዲሞክራቲክ ተፎካካሪው ጆ ባይደን ከተሸነፉ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ ቃል መግባት ያልፈለጉ ሲሆን የምርጫ ፉክክሩ መጨረሻ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እልባት እንደሚያገኝ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡
በምርጫው ቢሸነፉ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ያስተላልፉ እንደሆን በጋዜጠኞች ትናንት በኋይት ሀውስ የተጠየቁት የሪፐብሊካኑ ትራምፕ “ምን እንደሚከሰት እናያለን” ሲሉ መልሰዋል፡፡ ይህም ፕሬዝዳንቱ በምርጫው ቢሸነፉ እንኳን ወንበራቸውን ለመልቀቅ ሊያንገራግሩ እንደሚችሉ በብዙዎች ዘንድ የተፈጠረውን ስጋት እንደሚያባብስ እየተዘገበ ነው፡፡
በቅድመ ምርጫ በብሔራዊ ደረጃ በተሰበሰቡ ድምጾች በባይደን የሚመሩትፕሬዚዳንቱ በቀጣዩ ምርጫ ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው በተደጋጋሚ የሚገልጹ ሲሆን በፖስታ ድምጽ መስጠቱ ወደ ማጭበርበር እንደሚያመራ እና “የተጭበረበረ” ውጤት እንደሚያስከትል ያለ ምንም ማስረጃ ተናግረዋል ነው የተባለው፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ “የምርጫ ካርዶቹ አደጋ ናቸው” ስለማለታቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዴሞክራቶች በፖስታ ድምፅ መስጠትን የተሸለ አማራጭ አድርገው ደግፈዋል፡፡ ወታደራዊ ኃይሎችን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ለዓመታት ያለችግር በፖስታ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ 2016ም ትራምፕ የምርጫውን ውጤት ስለመቀበል አለመቀበላቸው ጥያቄ አንስተው ነበር ፡፡ ይሁንና በምርጫው ፕሬዝዳንቱ በማሸነፋቸው በዉጤቱ ላይ ጥያቄ አላነሱም፡፡
ጆ ባይደን ደላዌር ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ፣ ትራምፕ በሥልጣን ሽግግር ዙሪያ የሰጡት አስተያየት “ምክንያታዊ ያልሆነ” ነው ብለዋል ፡፡
የእሳቸው የምርጫ ዘመቻ ቡድን ከትራምፕ ለሚመጡ ማናቸውም “ድብቅና ህገወጥ ተግባራት” መዘጋጀቱን ያስታወቀ ሲሆን “የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ወንጀለኞችን ከኋይት ሀውስ ለማስወጣት ፍጹም ብቃት አለው” ሲል ከዚህ ቀደም ያቀረበውን ሀሳብ በድጋሚ አንስቷል፡፡
ትራምፕን ከሚተቹ ጥቂት የሪፐብሊካኑ ሴናተሮች መካከል አንዱ የሆኑት ሚት ሮምኒ በትዊተር ገፃቸው “ለዴሞክራሲ መሠረታዊ የሆነው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ነው ፤ … አንድ ፕሬዝዳንት ይህንን ህገ-መንግስታዊ ዋስትና አያከብርም የሚል ማንኛውም ሀሳብ የማይታሰብ እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕልባት ያገኘው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አንድ ብቻ ሲሆን ይኸውም እ.ኤ.አ. በ 2000 በሪፐብሊካኑ ጆርጅ ደብሊዩ ቡሽ እና በዴሞክራቱ አል ጎር መካከል የተካሄደው ምርጫ ነው፡፡