በኢትዮጵያ እየጨመረ ያለው አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እንደ አህጉር ቅናሽ ማሳየቱ ተነገረ
በኢትዮጵያ በወረርሽኙ የተያዙ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር የ5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ2 በመቶ የሚሞቱት ደግሞ በ17 በመቶ ቀንሷል ተብሏል
በኢትዮጵያ እየጨመረ ያለው አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እንደ አህጉር ቅናሽ ማሳየቱ ተነገረ
በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት 8 ቀናት ቀደም ሲል ባለፈው ሳምንት ከነበረው መቀነሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
ወረርሽኙን የተመለከተ የሁኔታዎች ዳሰሳ ሪፖርትን ዛሬ ያወጣው የድርጅቱ የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክቶሬት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ8 ቀናት በፊት ከነበረው በ2 በመቶ ቀንሷል ብሏል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ የመጨረሻውን የሁኔታዎች ዳሰሳ ሪፖርት ያወጣው እ.ኤ.አ መስከረም 16 ነበር፡፡
ከዛ ወዲህ ማለትም ከመስከረም 16 እስከ 22 ባሉት ተከታታይ 8 ቀናት ተጨማሪ 29 ሺ 218 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ተጨማሪ 764 ሰዎች መሞታቸውን ከ45ት የአህጉሪቱ ሃገራት የተጠናቀረውን መረጃ ይዞ ዛሬ የወጣው የዳሰሳ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ይህ ቀደም ባለው ሳምንት ማለትም ከመስከረም 9 እስከ 16 ባሉት ተከታታይ ቀናት ሪፖርት ከተደረገው በቫይረሱ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በቅደም ተከተል የ2 በመቶ እና የ17 በመቶ ቅናሽ ያለው ነው፡፡
ከመስከረም 9 እስከ 16 ባሉት ተከታታይ ቀናት 29 ሺ 710 አዳዲስ ኬዞች ሪፖርት ሲደረጉ 921 ሰዎች መሞታቸው ተገልጾ ነበር፡፡
ሪፖርት የሚደረገው የአዳዲስ ታማሚዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ከነበረውም ቅናሽ እያሳያ ይገኛል፡፡
ይህም በ29 የአህጉሪቱ ሃገራት ተስተውሏል፡፡ ከ29ኙ በ20ዎቹ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ20 በመቶ እና ከዚያ በላይ ቀንሷል፡፡
ዛሬ የወጣው ሪፖርት በተጠናቀረባቸው ያለፉት 8 ቀናት የሚያዙ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ሪፖርት ያደረጉ ሃገራትም ኢትዮጵያን ጨምሮ 16 ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር የ5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፡፡ ጤና ሚኒስቴር ትናንት መስከረም 13 ሪፖርት ባደረገው የ24 ሰዓታት መግለጫው በቫይረሱ የተያዙ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር 71 ሺ 83 መድረሱን አስታውቋል ተጨማሪ 661 ሰዎች በቫረሱ መያዛቸው መረጋገጡን በመጠቆም፡፡
በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ 150 የጤና ሰራተኞች መካከል 16ቱ በኢትዮጵያ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
ሪፖርቱ በተጠናቀረበት በዚሁ ሳምንት 764 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸው ከ27 ሃገራት ሪፖርት ተደርጓል የተባለም ሲሆን 92 ያህሉ (ከቁጥሩ 12 በመቶ) ከኢትዮጵያ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ይህም የሟቾቹ ቁጥር በኢትዮጵያ በ7 በመቶ መጨመሩን የሚያመለክት ነው፡፡
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአህጉሪቱ በቫይረሱ የተያዙ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር 1 ሚሊዬን 429 ሺ 704 መድረሱን እና 34 ሺ 839 ሰዎች መሞታቸውን የአፍሪካ ሲዲሲ ወቅታዊ መረጃ ያመለክታል፡፡