አብራሃም በላይ (ዶ/ር) የትግራይን ክልል በጊዜያዊነት ሲያስተዳድሩ የነበሩትን ሙሉ ነጋን (ዶ/ር) ተክተዋል
አብራሃም በላይ (ዶ/ር) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾመዋል፡፡
ዶ/ር አብራሃም ላለፉት 6 ወራት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩትን ዶ/ር ሙሉ ነጋን በመተካት በዋና ስራ አስፈጻሚነት መሾማቸውን የትግራይ ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር አረጋግጠዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉ ለምን ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ የተገለጸ ነገር የለም።
ዶ/ር አብራሃም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር። ዶ/ር አብራሃም የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትም ናቸው።
አቶ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር "መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንልዎት እመኛለሁኝ" ሲሉ ለዶ/ር አብራሃም
መልካም ምኞታቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል። ዶ/ር ሙሉ ነጋ ባሳለፍነው ወርሃ ህዳር መባቻ ነበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መሾማቸው ይታወሳል፡፡
ሹመቱ የፌደሬሽን ምክር ቤት በክልሉ የሚቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር አስመልክቶ ባጸደቀው ደንብ መሠረት የተሰጠ ነበር።
ሆኖም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የዶ/ር አብራሃም ሹመት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመሰጠቱ የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ዶ/ር ሙሉ ከአሁን ቀደምም ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩ ነበር።
መረጃዎቹን በማስመልከት አል ዐይን አማርኛ ላቀርብላቸው ጥያቄ "መነሳቴን አላውቅም" በሚል መረጃውን ማስተባበላቸው እና በስራ ላይ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክልሉ ጥሎት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትናንት መጠናቀቁ የሚታወስም ሲሆን ምክር ቤቱ ነገ በሚያደርገው መደበኛ ስብሰባ የአዋጁን ጊዜ ሊያራዝም እንደሚችልም ይጠበቃል።