ዩኬ በትግራይ ያለውን ግጭት ለማስቆም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን እንድታደርግ የሃገሪቱ ፓርላማ አሳሰበ
ሰብዓዊ እርዳታዎችን የሚያስተጓጉሉ ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይገባልም ነው ያለው
ፓርላማው የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ከጥቃቶች ለመጠበቅ ካልቻለ የዩኬ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድም አሳስቧል
የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት “ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን መጠቀም በትግራይ ያለውን ግጭት እንዲያስቆም” የሃገሪቱ ፓርላማ አሳሰበ፡፡
የፓርላማው የታችኛው ምክር ቤት (House of Commons) የዓለም አቀፍ ልማት ኮሚቴ በክልሉ ያለውን ግጭት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የዩኬ መንግስት አለበት ያለውን ኃላፊነት በተመለከተ ሪፖርት አውጥቷል፡፡
በሪፖርቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት ታጣቂዎች መካከል በመካሄድ ላይ ነው ባለው ጦርነት ምክንያት ምናልባትም በጦር ወንጀል ጭምር ሊያስጠይቁ የሚችሉ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየወጡ ነው ብሏል፡፡
ከአንዳንዶቹ ሰብዓዊ ጥሰቶች ጀርባ የኤርትራ ወታደሮች እጅ አለበት የሚሉ ክሶች ይደመጣሉም ብሏል፡፡
በመሆኑም የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ውጊያው እንዲያበቃ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ተጠቅሞ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሊያደርግ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘር ማጥፋት ስምምነቶች መሰረት የገባቸውን ግዴታዎች ሊያስታውስ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ኮሚቴው በሪፖርቱ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎች ሊበጁ እንደሚገባም ነው ያሳሰበው፡፡
ለዚህም መንግስት ከተመድ፣ ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና በግጭቱ ተሳታፊ ከሆኑ አካላት እንዲሁም ከጎረቤት አገራት ጋር አብሮ መስራት ይገባዋል ብሏል።
ሰብዓዊ እርዳታዎችን የሚያስተጓጉሉ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የአሰራር ሂደቶች መሰረት ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይገባልም ነው ያለው፡፡
ኮሚቴው ተፈጽመዋል በተባሉ ሰብዓዊ ጥሰቶች እጅግ ማዘኑን ገልጾ ጥሰቶቹ በገለልተኛ አካል ተመርምረው ወንጀለኞች ሊጠየቁ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ከጥቃቶች ለመጠበቅ ካልቻለ የዩኬ መንግሥት በዘር ማጥፋት ስምምነቶች መሰረት ተገቢውን እርምጃ መውሰዱን እንዳይዘነጋም አስጠንቅቋል፡፡
የውጭና፣የኮመንዌልዝ እና ልማት ቢሮ (FCDO) ለሃገራት በሚያዘጋጀው ወቅታዊ ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ እና ለጎረቤቶቿ የሚሆን የግፍ ግድያ መከላከያ ስትራቴጂን ሊያካትት ይገባልም ብሏል፡፡
በትግራይ ተፈፅሟል የተባለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከአፍሪካ ህብረት እና ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለመምረመር ከስምምነት መደረሱ የሚታወስ ነው፡፡
በመደረግ ላይ ካሉ ሰብዓዊ እርዳታዎች አብዛኞቹ (ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት) በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈኑ ናቸው መባሉም ይታወሳል፡፡
ቀደም ባሉት ሳምንታት በነበሯቸው ሳምንታዊ መግለጫዎች ስለዚሁ ጉዳይ ተደጋጋሚ ማብራሪያን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሃገራት በሚሉት ልክ ድጋፍ እያደረጉ እንዳልሆነ መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡