የግንቦቱ “ምርጫ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ከሚበሰርባቸው ምዕራፎች አንዱ ነው”-ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት በመጪው ክረምት ለመፈጸም ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ጠቁመዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል የምናከብረው በተስፋና በተጋድሎ መካከል ውስጥ ሆነን ነው”ም ብለዋል
“የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል የምናከብረው በተስፋና በተጋድሎ መካከል ውስጥ ሆነን ነው” ሲሉ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል አስመልክተው ሃይማኖታዊ አንድምታዎችን የሚያጣቅስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸው የዘንድሮው በዓል “በተስፋና በተጋድሎ መካከል ውስጥ ሆነን” የምናከብረው ነው ብለዋል፡፡
“በአንድ በኩል የሀገራችንን ትንሣኤ አሻግረን እያየን በተስፋ፣ በሌላ በኩል ከፊታችን የተደረደሩ ፈተናዎች ከትንሣኤው እንዳያስቀሩን ከባድ ትግል እያደረግን ነው”ም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት።
ለብዙዎች ባይታይም የኢትዮጵያ ትንሣኤ “እውን ከመሆን የሚቀር አይደለም”ም ብለዋል።
ትንሳዔው ከሚበሰርባቸው ምዕራፎች መካከል አንዱ በመጪው ግንቦት የሚካሄደው 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ እንደሆነም አስቀምጠዋል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ ምርጫው “ለዘመናት ስንናፍቅ ኖረናል” ያሉለት ዴሞክራሲ የሚፈነጠቅበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
“የሕዳሴ ግድባችን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል”ም ብለዋል የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት በመጪው ክረምት ለመፈጸም ዝግጅቶች መደረጋቸውን በመጠቆም፡፡
ሆኖም “ፈተናዎች በርትተው” መቆየታቸውንም አልሸሸጉም፡፡
“ምርጫ ለማድረግ እና ግድባችንን በስኬት ሞልተን ለማጠናቀቅ ከጊዜና ከሁኔታዎች ጋር ትግል ስናደርግ፣ ፈታኞቻችንም በሌላ አቅጣጫ እኛን የሚያሰናክሉበትን የመጨረሻ ድንጋይ ከመወርወር እንደማይቆጠቡ መዘንጋት አይገባም” ም ብለዋል።
“ዛሬም በመንገዳችን ላይ አደጋ እየጣሉ” ነው ያሏቸው ሽፍቶች ሃገራዊ ትንሳዔው እንዳይሳካ የቻሉትን እንደሚያደርጉ እና እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።
የዜጎች ግድያና መፈናቀልንም በማሳያነት አስቀምጠዋል፡፡ ሆኖም “በድርጊታቸው የክፋታቸውን ጥግ ከመግለጥ ውጭ በዚያ መንገድ የሚያሳኩት አንድም ዓላማ የለም” እንደ ዶ/ር ዐቢይ ገለጻ።
ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታም “በውዥንብርና በተስፋ መካከል የምትዋዥቅ” ባሏት በዛሬዋ ዕለት በቅዳሜ (በቅዳም ስዑር) መስለውታል።
ነገር ግን “ከከበቧት መከራዎች፣ ግድያዎች፣ ውዥንብሮችና ጩኸቶች በላይ ናት”ና ሁሉን አሸንፋ ትነሣና ጠላቶቿን ሁሉ ታሳፍራለች ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
“የተፈጸሙብን ግፎችና፣ የተደረጉብን ስቅላቶች ሁሉ ኢትዮጵያን ለማቆም ያሰቡ መሆናቸውን ትውልድ ሁሉ በግልጥ ይረዳል”ም ብለዋል።