የዓለም የኃይል ጉባኤ በአቡ ዳቢ ተጀመረ
ጉባኤው በፈረንጆቹ 2023 በተለይ የኃይል ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ተነግሯል
አረብ ኤምሬትስ ቀጣዩ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የተግባር እና የግብ ጉባኤ እንዲሆን እንፈልጋለን ብላለች
በአትላንቲክ ካውንስል የተዘጋጀው ሰባተኛው የዓለም የኃይል ጉባኤ በአረብ ኢምሬትስ አቡ ዳቢ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ላይ ለቀጣዩ ዓመት ዓለም አቀፍ የኃይል አጀንዳ እና የሽግግር ገጽታ ለመቅረጽ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የኃይል መሪዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 28) ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃበር የከባቢ ሙቀትን ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ለማድረስ በፈረንጆቹ 2030 ልቀት በ43 በመቶ መቀነስ አለበት ብለዋል።
- አረብ ኤምሬትስ ሱልጣን አል ጀበርን የ28ተኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፕሬዝዳንት አድርጋ ሾመች
- ዩኤኢ የ2023ቱ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ አስተናጋጅ ሆና ተመረጠች
አክለውም ቀጣዩ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የተግባር እና የግብ ጉባኤ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል። "ከታዳሽ ምንጮች የሚገኘውን የኃይል ምርት በእጥፍ ማሳደግ አለብን" ሲሉም አክለዋል።
"ከነፋስ እና ከጸሀይ የሚመነጨው ኃይል በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከፍ ማለቱን ይቀጥላል" ብለዋል አል ጀበር።
በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ (ኮፕ 28) ጉባኤ ከአየር ንብረት እና የኃይል ስልት ጋር በተያያዙ ወሳኝ ጉዳዮች ቀዳሚ በመሆናቸው በዘንድሮው ጉባኤ ልዩ ጠቀሜታ አላቸው ተብሏል።
ጉባኤው በ2023 መጨረሻ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
የዓለም የኃይል ጉባኤ በ2023 በተለይ የኃይል ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮችን ለመቆጣጠር፣ የካርቦን ልቀትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት እንዲሁም ለአየር ንብረት እርምጃ የሚደረጉ ጥረቶች እና ሀገራት "የተጣራ ዜሮ" የካርበን ልቀትን ለመድረስ በሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ላይ እንደሚያተኩር ተነግሯል።