የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በግላስኮው የተደረሰው ስምምነት ምን የሚል ነው?
ስምምነቱ፤ አሁንም ለተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች መጋለጣችን ቀጥሏል ያሉ አዳጊ ሃገራትን አላጠገበም
የግላስኮው የአየር ንብረት ስምምነት በጉባዔው ሲሳተፉ በነበሩ ከ200 በላይ ሃገራት ተፈርሟል
እየከፋ መጥቷል የተባለውን የአየር ንብረት ለውጥ በተመለከተ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በስኮትላንድ ግላስኮ ስትመክር የነበረችው ዓለም ለውጡን ለመቋቋም ከታመነበት ስምምነት ላይ መድረሷ ተነግሯል፡፡
ስምምነቱ የግላስኮው የአየር ንብረት ስምምነት (Glasgow Climate Pact) የሚል መጠሪያ አለው፡፡
በጉባዔው (ኮፕ26) ሲሳተፉ በነበሩ ከ200 በላይ ሃገራት ተፈርሟል ነው የተባለው፡፡
ዩኤኢ የ2023ቱ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ አስተናጋጅ ሆና ተመረጠች
ለመሆኑ ስምምነቱ ምን ለማድረግ ነው የተፈረመው?
የ2015ቱን የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን ጨምሮ ከአሁን ቀደም በተደረሱ ስምምነቶች እና በተገቡ ቃሎች ዙሪያ ያለፉትን ሁለት ሳምንታት ሲከራከሩ የቆዩት የኮፕ26 ተሳታፊ ሃገራት ደረስንበት ያሉት አዲስ ስምምነት የዓለምን አማካይ የሙቀት መጠን ከ1.5 °C እንዳይበልጥ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ለተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች በመጋለጥ ላይ ያለችው ዓለም አሁን ላይ አማካይ የሙቀት መጠኗ እጅግ እየጨመረ ነው ይባላል፡፡ ይህ እጅግ አደገኛ ከመሆንም በላይ ለተለያዩ የከፉ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጋልጥ ነው፡፡
ይህን ለመቋቋምም ነው ሃገራቱ ከ1.5 °C በታች ለማድረግ ወደሚያስችል ተገባር መግባት አለብን ሲሉ የተስማሙት፡፡
ሆኖም ይህ አደግን ከሚሉት ሃገራት ኢንዱስትሪዎች የሚወጣውን የበካይ ጋዝ ልቀት መቀነስንና አረንጓዴ ልማትን ማጠናከርን ይጠይቃል፡፡ በተግባር የተደገፈ ቁርጠኝነትን የግድ የሚልም ነው፡፡
የድንጋይ ከሰል አገልግሎት ማብቃት አለበት በሚል ሲደረግ የነበረው ክርክርም ቀላል አልነበረም፡፡ ህንድን መሰል ሃገራት ይህን መባሉን ተቃውመው በስምምነቱ አንቀጾች የተካተቱ ቃላት ላይ ለውጥ እንዲኖር አድርገዋል፡፡
ስምምነቱ አሁንም የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ለተለያዩ አደጋዎች ለተጋለጡ ሃገራት አጥጋቢ አይደለም፡፡ እየገጠመን ላው ችግር ተገቢው ትኩረት አልተሰጠም በሚል ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡
አንዱ የሃገራቱ ጥያቄ ከአሁን ቀደም በየዓመቱ ለመስጠት ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ አልተፈጸመም የሚል ነው፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ለሆኑ ሃገራት ከባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2020 ጀምሮ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ለመደጎም ቃል ተገብቶ ነበር፡፡ ሆኖም አልተፈጸመም፡፡ አሁን ግን ቃሉን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ለባለፉት ሁለት ሳምንታት በስኮትላንድ ግላስኮው ሲካሄድ የነበረው ኮፕ26 ትናንት ቅዳሜ ህዳር 4 ቀን 2014 ዓ/ም ተጠናቋል፡፡ ጉባዔው ከተያዘለት እቅድ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው የተጠናቀቀው፡፡
በኮፕ26 ከ200 መቶ በሚልቁት ተሳታፊ ሀገራቱ የተፈረመውን ስምምነት ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ግብጽ ኮፕ28ን እና ኮፕ27ን እንዲያዘጋጁ በጉባዔው መመረጣቸውም የሚታወስ ነው፡፡