ፋሲል ከነማ አራት ጨዋታ እየቀረው ነው የ2013 የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው
በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ 20 ጨዋታዎችን አድርጎ 49 ነጥቦችን የሰበሰበው ፋሲል ከነማ አራት ጨዋታ እየቀረው ነው የ2013 የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ዲቻ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት የሊጉ ጨጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል ከነማ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል። በ35 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ፋሲልን የሚከተለው ቡና ከዲቻ ጋር ያለግብ ነው ጨዋታውን ያጠናቀቀው፡፡
ባለድሉ ፋሲል በቀጣዩ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፍ ይሆናል፡፡ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ክለብ ፣ በሌላኛው የአህጉሪቱ መድረክ-ኮንፈዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክል ይሆናል፡፡
ፋሲል ከነማ በኮሮና ምክንያት በተቋረጠው ባለፈው የውድድር ዓመትም ዋንጫውን ለማሸነፍ ተቃርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የዓመቱ ውድድር ሳይጠናቀቅ እንዲቋረጥ በመወሰኑ ያለፈው ዓመት ማንም ሻምፒዮን ሳይሆን ተዘግቷል፡፡