ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀሌ ገብተዋል
ፖትርያርኩ ወደ በመቀሌ ያቀኑት በአቡነ ዮሐንስ ዳግማዊ የቀብር ሰነ ስርአት ላይ ለመገኘት መሆኑ ተገልጿል
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በትግራይ የሚገኙ ሊቃነጳጳሳት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀሌ ገብተዋል።
ፓትርያርኩ ወደ መቀሌ ያቀኑት ከቀናት በፊት ህይወታቸው ባለፈው በብጹእ አቡነ ዮሐንስ ዳግማዊ የቀብር ስነ-ስርአት ላይ ለመገኘት እንደሆነም የትግራይ የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡
- ተወግዘው የነበሩት አባቶች ስምምነቱ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር መስማማታቸውን ቤተክርስቲያኗ አስታወቀች
- "አዲስ ሲኖዶስ" በሚል የተቋቋመው አካል በኃላፊዎች ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል ቤተክርስቲያናትን መቆጣጠሩን ኢሰመኮ ገለጸ
ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመቀሌ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ አባት ናቸው፡፡
በትግራይ የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መለየታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
"መንበረ-ሰላማ ከሳቴብርሃን ቤተክህነት" የሚል መጠሪያ ያለው ቤተክህነት አቋቁመውም አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
የትግራይ አባቶች ከቅዱስ ሲኖዶሱ ለመለየታቸው ቤተክርስቲያኗ በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ህዝብ የደረሰበትን በደል ላለማንሳት ዝምታን መርጣለች የሚል ምክንያት ያቀርባሉ።
የፌደራል መንግስት እና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ ስምምነት ደርሰው ጦርነቱም ጋብ ሲል የሻከረውን ግንኙነት የማደስ ጥረት ሲደረግ ታይቷል።
በየካቲት ወር መግቢያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ ትግራይ የላከው ደብዳቤም ተቋርጦ የቆየው ግንኙነት እንዲቀጥል የሚጠይቅ ነበር።
ደብዳቤው “ጦርነቱ አላስፈላጊና በወንድማማቾች መካከል የተካሄደ፣ የከበደ የህይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ያደረሰ” መሆኑን አስታውሶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተከሰተው ሁሉ ማዘኗን ይገልፃል።
ቤተክርስያኗ በጊዜው ሀዘኗን ባለመግለጿና ድርጊቱን ባለማውገዟ ትግራይ ባሉ የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች ዘንድ የተፈጠረው ቅሬታ ተገቢ ስለመሆኑም ያነሳል ደብዳቤው።
የካቲት 10 2015 በትግራይ የሚገኙ ሊቃነጳጳሳት በሰጡት መግለጫ ግን ከቅዱስ ሲኖዶሱ የተላከውን የግንኙነት እናድስ ደብዳቤ እንደማይቀበሉት ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ደብዳቤው የተላከው ትግራይ ውስጥ ለሚገኙ አምስት ሊቃነጳጳሳት ብቻ መሆኑና ላቋቋሙት "መንበረ-ሰላማ ከሳቴብርሃን ቤተክህነት" አለመድረሱን በማንሳትም ጥሪውን እንደማይቀበሉት መግለጻቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መቀሌ መግባታቸውም ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት ለማለዘብ እንደሚረዳ ታምኖበታል።