የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንግስትን ከሰሰች
ቤተ ክርስቲያኗ የቀድሞ ሶስት ጳጳሳትና የተሾሙት 25 ጳጳሳትንም ከሳለች
የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ላይም ቤተ ክርስቲያኗ ክስ አቅርባለች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት እና ተቋማት ላይ ክስ መመስረቷን በዛሬው እለት አስታውቃለች፡፡
የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ከህግ ባለሙያዎች ጋር በመሆን በዛሬው እለት በጠቅላይ ቤተ ክህነት መግለጫ ሰጥተዋል።
- ቤተክርስቲያኗ ካወገዘቻቸው "ቡድኖች" ጋር እኩል መታየቷን ተቃወመች
- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተፈጠረው ችግር ላይ የመንግስት ምላሽ ምን ይሆናል?
በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አቤቱታዋንለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ መሰረታዊ እና ነጻነት መብቶች ምድብ ችሎት ማቅረቧን አስታውቃለች።
በዚህ ክስም በቀድሞ ስማቸው አባ ሳዊሮስ፣ አባ ኤዎስጣጢዮስ፣ አባ ዜና ማርቆስ እንዲሁም የጵጵስና ሹመት ተቀብለው የነበሩ 25 ግለሰቦች ክስ እንደቀረበባቸው ተነግሯል።
በተጨማሪም የቡድኑን ወክለው በተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጡ የነበሩ ጠበቃ ኃለሚካዔል ታደሰ በግጭት ቀስቃሽ መልእክት በማስተላለፍ ክስ እንደቀረበባቸው ተመላቷል።
እንዲሁም፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ላይ ክስ መቅረቡን ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው የቆሙ ጠበቆች አስታውቀዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በክሷ የቤትክርስቲያንን ክብርና ስም በመንካት፣ በህይወት የመኖር፣ የመዘዋወር እና የማምለክ መብትን በመከልከል እንዲሁም መንግስት ሁሉን ሰው በእኩል ህጋዊ ጥበቃ እና በእኩልነት የማየት ህገመንግስታዊ ሀላፊነትን ባለመወጣት የሚሉ ይገኙበታል።
በተጨማሪም የቤተክህነት ንብረት ሲዘረፍ እርምጃ ባለመውሰድ፣ ጳጳሳትን እና የቤተክህነት ህጋዊ መዋቅር ውስጥ ያሉትን በማፈን፣ በማሰርና በማስፈራራት እና የመንግስት ሚዲያ በህዝብ ሀብት እየተዳደረ የቤተክርስቲያኗን መግለጫ እና የደረሰባትን የህግ ጥሰት ባለመዘገብ ህገመንግስታዊ ሀላፊነትን ባለመወጣት የሚለውም ተካቷል።
ከክስ ሂደቱ አስቀድሞ ጊዜያዊ እግድ እንዲሰጥ ለፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ችሎት አቤቱታ መቀረቡን ጠበቆቹ አስታውቀዋል።
በዚህም ህገወጡ ቡድን ወደ ቤተክርስቲያን ቅጥር እንዳይደርስ፣ ንብረት እንዳያንቀሳቅስ፣ የቤተክርስቲያኗ ጥቅምና መብት እንዲከበር ይህ ክስ በዝርዝር እስኪታይ እግድ ትዕዛዝ እንዲተላለፍ ቤተክርስቶያኗን የወከሉት ጠበቆች ፍርድቤትን ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ከቤተ ክርስቲያኗ ህግ ውጪ ተካሂደዋል ባለቻቸው የጵጵስና ሹመቶች ዙሪያ ውሳኔ ማሳለፏ ይታወሳል።
በዚህ መሰረትም 1ኛ አባ ሳዊሮስ፣ 2ኛ አባ ኤዎስጣቴዎስ እና 3ኛ አባ ዜና ማርቆስ ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ መነሳቱ ተገልጿል።
ሶስቱ የቤተክርስቲያኗ የሀይማኖት አባት የነበሩት ሰዎችም ከጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ መወሰኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ማሳወቁ ይታወሳል።