ቤተክርስቲያኗ ተወግዘው ከነበሩት አባቶች ጋር የደረሰችው ስምምነት ተጥሷል አለች
ስምምነቱ በሁለት ቀኑ መጣሱን ቤተክርስቲያኒቱ ማምሻውን በሰጠችው መግለጫ አስታውቃለች
ዛሬ ቤተክህነት የገቡት የቀድሞ አባቶች "አቋማቸውን ካላስተካከሉ" ከቤተክህነት እንዲወጡ ተጠይቀዋል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከቀናት ንግግር በኋላ አፈንግጠው የራሳቸውን ሲኖዶስ አቋቁመናል ካሉ የቀድሞ አባቶች ጋር የካቲት ስምንት የደረሰችው ስምምነት መጣሱን አሳወቀች።
ቤተክርስቲያኒቱ በሰጠችው መግለጫ "ቀኖናዬ ዳግም ተጥሷል" ብላለች።
ቤተክርስቲያኗ ይህን ያለችው ተወግዘው የነበሩት አባቶች በተደረሰው ስምምነት መሠረት ቤተክህነት ገብተው በሰጡት መግለጫ 'ቀኖና አልጣስንም' ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
ችግሩን በቀኖናዋ መሠረት መፍታቷን እና ህገወጥ የተባለውን ሲመት የሰጡ እና የተቀበሉት አባቶች ወደ ቀድሞ የአገልግሎት ቦታቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ቤተክርስቲየኗ ገልጻ ነበር።
ነገርግን ስምምነት ፈጽመው የነበሩት አባቶች ቀኖና አልጣስንም የሚል መግለጫ መስጠታቸው ድጋሚ ችግር ተቀስቅሷል።
ጥር 14፣2015 ዓ.ም ሦስት ጳጳሳት በደቡብ ምዕራብ ሽዋ ሀገረስብከት 25 ኤጲስ ቆጶሳት ሾመናል ማለታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓቷና ህጓ መጣሱን አሳውቃለች።
ቤተክርስቲያኗ አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምላተ ጉባኤ አድርጋም ሲመት የሰጡትን እና የተቀበሉትን በሙሉ ከቤተክርስቲያን እንዲለዩ እና እንዲወገዙ ውሳኔ ማሳለፏ አይዘነጋም።
በየካቲት ስምንቱ ስምምነት የቀድሞ አባቶች ይቅርታ ጠይቀው 10 ነጥብ መፍትሄዎች ላይ ተስማምተናል ብለዋል።
የጠቅላይ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ አቡነ አብርሃም የጳጳሳቱ ሹመት እንደተጠበቀ ነገር ግን ተሾሙ የተባሉት ኤጲስ ቆጶሳት ሲመት እንደሚሻር ተስማምተን የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን "ስምምነቱን ገቢራዊ አላደረጉም" ሲሉ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
ለዚህ ማስረጃ ሲያጣቅሱ ዛሬ የካቲት 10 ከቀትር በኋላ የተወገዙት አባቶች የሰጡትን መግለጫንና አልባሳቶቻቸውን አንስተዋል። በዚህም "ቀኖና አልጣስንም" ማለታቸውና ጵጵስናቸው የተሰረዘባቸው ተሿሚዎች ያልተፈቀዱ አልባሳትን ለብሰው መታየታቸው ተገልጿል።
አቡነ አብርሃም እርምጃውን "ህግን የጣሰ፤ ስምምነቱን ያፈረሰ" ነው ያሉ ሲሆን፤ "በቃ ሊባል ይገባዋልም" ብለዋል።
ሲመተ ጵጵስና አደረግን ያሉ የቀድሞ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ጥያቄ ከኃይማኖታዊነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘቱ የላቀ ነው ሲሉም የጠቅላይ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ ተናግረዋል።
"ኃይማኖትን ለመበረዝ ታጥቀው መነሳታቸውን አሳውቀዋል። አቋማቸውን እስካላስተካከሉ ድረስ ከቤተክህነት ይውጡልን" ሲሉም ተናግረዋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ አቡነ ጴጥሮስ በበኩላቸው "ስጋዊ ጥያቄ" ተነስቷል ነው ያሉት። "ጥያቄያቸው ቤተክርስቲያንን የሚመለከት ሳይሆን ሙልጭ ያለ ፖለቲካ ነው። ኃይማኖት፣ ቀነኖ፣ ዶግማና መንፈሳዊ አይደለም። ስጋዊ አስተሳሰብ ነው" ብለዋል።
ለቀድሞ አባቶች ውግዘቱ እንዲነሳና ወደ አገልግሎት እንድትመለሱ ስምምነቱን እንዲያከብሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናንና ደጋፊዎች ከመደነጋገር ይልቅ በትዕግስት እንዲጠብቁ ጥሪ ቀርቧል።
በየካቲት ስምንቱ ስምምነት በዋናነት ከቋንቋና ከአገልጋዮች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስና የተጀመሩ ጥረቶችን ማጠናከር አጽንኦት ተሰጥቶታል።