ለ12 አመታት የየኔ ቢጤ ገጸባህሪን ተላብሶ በመተወን ሃብት ያፈራው ቻይናዊ
በወር 10 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ገቢ የሚያገኘው ግለሰብ ፈተና ወደሚበዛበት የፊልም ትወና መመለስ አልፈልግም ብሏል
ግለሰቡ “እንደኔ መተወን ስለማትችሉ ወዳለሁበት መጥታችሁ ልመናን አትሞክሩት” ሲል መክሯል
በቻይና ሄናን ግዛት ነዋሪ የሆነው ሉ ጂንጋንግ የፊልም ትወና ትምህርት ተከታትሎ ተመርቋል።
ሉ ጂንጋንግ በትወና ሙያው ፊልም አልያም ድራማ ግን አልሰራም።
ለትወና ብቁ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ተደጋጋሚ ፈተናዎችን አልፎ በተማረበት ሙያ ለመስራት እንደማይችል ሲረዳ ግን አንድ ነገር ወደ አዕምሮው መጣ። ለምን ሙያዬን ለልመና አልጠቀምበትም የሚል ሃሳብ።
የየኔ ቢጤ ገጸባህሪን ተላብሼ በመጫወት ሊሳካልኝ ይችላል በሚልም ከ12 አመት በፊት በኪያፌንግ ከተማ ጎብኝዎች በሚያዘወትሩት የባህር ዳርቻ መዝናኛ “ትወናውን” ጀመረ።
በገሃዱ አለም ከሰዎች ምጽዋት የማይፈልገው ሉ ፊቱን ጭቃ ቀብቶ፤ የተቀዳደዱ ልብሶችን ለብሶ፤ ጎብኝዎችን ወደኪሳቸው የሚያስገቡ አሳዛኝ ቃላትን በማውጣት ትወናውን ተያያዘው።
የትወና ሙያው ያገዘው ቻይናዊ በወር እስከ 70 ሺህ ዩዋን (9 ሺህ 730 ዶላር) ማግኘት መጀመሩም የተላበሰውን ገጸባህሪ መስሎ ሳይሆን ሆኖ ይበልጥ አበረታታው።
ታይም ዶክተር የተሰኘው ድረገጽ መረጃ እንደሚያሳየው የቻይናውያን አማካይ ወርሃዊ ገቢ 4 ሺህ ዶላር ገደማ ነው።
ይህም የኔ ቢጤ መስሎ የሚተውነውን ሉ በእስያዊቷ ሀገር ከፍተኛ ገቢ ከሚያገኙ ሰዎች ተረታ መሰለፉን ያሳያል። አንዳንዶችም በቻይና ሀብታሙ የኔ ቢጤ ነው ብለው እስከመጥራት ደርሰዋል።
ሉ ጂንጋንግ ግን ይህን ስያሜ አይቀበለውም፤ የትወና ብቃቱን ተጠቅሞ ገንዘብ እየሰራ መሆኑን ያምናል።
“ትወናውን” እንደጀመረ ከቤተሰቦቹ ጭምር ተቃውሞ ይገጥመው እንደነበር የሚያስታውሰው ሉ፥ ወርሃዊ ገቢውን ሲመለከቱ ሃሳባቸውን መለወጣቸውን ይገልጻል።
ገቢው ይፋ ከተደረገ በኋላ በቻይና ማህበራዊ ሚዲያዎች መከራከሪያ አጀንዳ የሆነው ግለሰቡ፥ ትችቱ ቢበዛበትም በባህር ዳርቻው በየቀኑ መተወኑን ቀጥሏል።
የሚያገኘውን ገቢ የሰሙ ሰዎች ወደሚገኝበት ስፍራ በማቅናት ለመለመን እንዳይሞክሩም ነው የመከረው።
ከአለባበሱ ጀምሮ ከቆሸሸ ፊቱ ላይ የሚታየው ሀዘን እና ልብ የሚያራሩ ቃላቱ በልማድ ሳይሆን በተደጋጋሚ ልምምድና የትወና ብቃት የተገኙ መሆናቸውን በመጥቀስም “ጊዜያችሁን አታጥፉ” ብሏል።
ከገሃዱ ኑሮው በተቃርኖ የሚገኝ ገጸባህሪን ተላብሶ በመጫወት ከፍተኛ ገቢ እያገኘ ያለው ሉ ጂንጋንግ ብዙ ድካምና ፈተና ወዳለበት የፊልም ትወና ሙያ አልመለስም ማለቱንም ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
ዜናው ከተሰማ በኋላ “እንዴት በልመና ይተወናል?” የሚሉና “ሙያውን ተጠቅሞ ገንዘብ መስራቱ ካላስቀናን በስተቀር ምንድን ነው ጥፋቱ?” በሚሉ ሁለት ጎራዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
የእርሶስ ሃሳብ ምንድን ነው?