ትዳርን የሚፈሩ ቻይናዊያን ሴቶች ቁጥር ለምን እየጨመረ መጣ?
በቻይና 32 ሚሊዮን ወንዶች ሚስት ማግባት ቢፈልጉም የሴት እጥረት አለባቸው ተብሏል
የተማሩ እና የተሻለ ኢኮኖሚ ያላቸው ሴት ቻይናዊያን ቁጥር ከወንዶች ቁጥር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑ ሴቶች ትዳርን ምርጫቸው እንዳይሆን ማድረጉ ተገልጿል
ትዳርን የሚፈሩ ቻይናዊያን ሴቶች ቁጥር ለምን እየጨመረ መጣ?
ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ቻይና ዓለማችን ቁጥር አንድ ባለ ብዙ ህዝብ ቁጥር ሆኖ ቆይታ ባለፈው ዓመት ደረጃዋን ለሕንድ አስረክባለች፡፡
ለቻይና የህዝብ ቁጥር መቀነስ ትዳር የሚይዙ እና ልጆችን የሚወልዱ ዜጎች ቁጥር መቀነስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎ የቻይና መንግስት ዜጎቹ ትዳር እንዲመሰርቱ እና ልጆችን እንዲወልዱ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ቢዘረጋም በተለይ ሴት ቻይናዊያን ትዳር ለመመስረት ያላቸወ ፍላጎት እየቀነሰ መምጣቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በቻይና “አናገባም፣ ልጅም አንወልድም” የሚል የሴቶች ንቅናቄ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ለዚህ ዋናው ምክንያታቸው የተባለው የኑሮ ውድነት ነው ቢባልም እውነተኛው ምክንያት ሴቶች ከወንዶች አንጻር የተማሩ እና የተሻለ የኑሮ ደረጃ መያዛቸው እንደሆነ የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡
ቻይና ትዳር የመሰረቱ ዜጎቿን እንደምትሸልም ገለጸች
በካሊፎርኒያ ዩንቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማራው ፕሮፌሰር ሾሊንግ ሱ እንዳሉት የተማሩ እና ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ቻይናዊያን ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሴቶች እና ወንዶች መካከል ያለው የገቢ ልዩነት እና የኑሮ መራራቅ ቻይናዊን ሴቶች የሚመጥናቸውን ባል ለማግኘት መቸገራቸውንም ተመራማሪው ጠቅሰዋል፡፡
32 ሚሊዮን ቻይናዊያን ወንዶች ማግባት ቢፈልጉም የሴቶች እጥረት አለ የሚሉት ፕሮፌሰር ሾሊንግ ሴቶች ልጅ ከመውለድ እና ትዳር መያዝን ደስታ ለማጣታቸው ምክንያት ነው ብለው ከማሰባቸው ጋር ተደማምሮ የሀገሪቱን ህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
ቻይ ዋንሩ የተሰኘች ቻይናዊ ለምን ትዳር የመመስረት ፍላጎት እንዳጣች ስትናገር “ከእኛ በፊት የነበሩት ሴቶች በማግባታቸው ከደስታ ይልቅ ብዙ ስቃዮችን አሳልፈዋል፣ ትዳር በመያዛቸው ያሰቡትን ደስታ ማግኘት አልቻሉም“ ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡
በቻይና አማካኝ የጋብቻ መመስረቻ ዕድሜ 28 ዓመት ላይ የደረሰ ሲሆን እድሜያቸው ለጋብቻ የደረሱ ነገር ግን ያላገቡ ዜጎች ቁጥርም 239 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
የቻይና መንግስት ጋብቻን እና የሚወለዱ ልጆችን ለማበረታታት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ በመተግበር ላይ ቢሆንም በተከታታይ ዓመታት የሚለዱ ህጻናት ቁጥር እየቀነሰ ይገኛል፡፡
ይሁንና ቻይናዊያን ሴቶች ለጋብቻ ራሳቸውን ከማዘጋጀት ይልቅ የተለያዩ የዓለማችንን ሀገራት ለመጎብኘት ገንዘብ መቆጠብ ላይ የተጠመዱ ዜጎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ በዘገባው ላይ ተገልጿል፡፡