ምግብ ከቆሻሻ ገንዳ የመሰብሰብ ልማድ የተጠናወታቸው ሚሊየነር
የ80 አመቱ ጀርመናዊ ገጽታቸው ጎዳና ተዳዳሪ ቢያስመስላቸውም ዘጠኝ ቤቶች ገዝተው አክራይተዋል ተብሏል
“ሰዎች ምግብ ከሚበቃቸው በላይ ገዝተው ይጥሉታል” የሚሉት አዛውንት ወርሃዊ ወጪያቸው ከ10 ዩሮ አይበልጥም
ጀርመናዊው አዛውንት ሄንዝ ቢ የአለማችን “ስስታሙ ሚሊየነር” ተሰኝተዋል።
የ80 አመቱ አዛውንት በሚሊየን የሚቆጠር ሃብት ቢኖራቸውም ያጣ የነጣ ምስኪን ድሃ ነው የሚመስሉት።
ሄንዝ ዘወትር ምግባቸውን ከቆሻሻ ገንዳ የመሰብሰብ ልማዳቸውና አለባበሳቸው ሁለት አፓርትመንትና ሰባት ቤቶች በስማቸው የገዙ በፍጹም አያስመስላቸውም ይላል የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ።
በደቡብ ምዕራባዊ ጀርመን ዳርምሽዳት ነዋሪ የሆኑት ሄንዝ በርግጥ የባንክ ሂሳብ ደብተራቸው ላይ ያላቸው 15 ዩሮ ብቻ ነው።
ይህም በቅርቡ 10ኛ ቤታቸውን ለመግዛት 700 ሺህ ዩሮ ከሂሳባቸው ላይ በመውጣቱ ነው የሚለው ቢልድ ጋዜጣ፥ 100 ሺህ ዩሮም በማይንቀሳቀስ የሂሳብ ደብተር አስቀምጠው በየጊዜው ወለድ እንደሚወስዱ ጠቅሷል።
የቀድሞው የኤሌክትሪክ ኢንጂነር በቴሌኮምዩኒኬሽን ቢሮ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመስራታቸው በየወሩ 3 ሺህ 600 ዩሮ ጡረታ ያገኛሉ።
“ለምግብ በወር 5 ዩሮ እንኳን አውጥቼ አላውቅም” የሚሉት አዛውንቱ፥ ከፍተኛ ወርሃዊ ወጪያቸው 10 ዩሮ ነው (ለላፕቶፕ ኮምፒውተራቸው ኢንተርኔት እና ለስልካችው ወርሃዊ ኪራይ የሚከፍሉት)።
ለምግብ ገንዘብ አውጥቶ ለመግዛት እጄ የሚያጥረው “ከአስተዳደጌ” የተነሳ ነው በማለትም “ስስታሙ ሚሊየነር” በሚል የተሰጣቸውን ቅጽል ስም እንደሚቀበሉት ይናገራሉ።
“ገንዘብ አውጥቼ ምግብ ለመሸመት ባስብ እንኳን በቆሻሻ ገንዳ የሚጣለውን ምግብ አይና ሃሳቤን እቀይራለሁ፤ ሰዎች ከሚያስፈልጋቸው በላይ ምግብ ገዝተው ሳይጠቀሙት ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ይጥሉታል” ሲሉም ለቢልድ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
ሄንዝ ምግብ ብቻ አይደለም ይጠቅማል ያሉትን ነገር ሁሉ በአሮጌ ብስክሌታቸው ጭነው የመጓዝ ልማድም አላቸው።
ብቸኛ መንቀሳቀሻ ብስክሌታቸውን እያከራዩ በምትኩ ምግብ የሚያገኙት የ80 አመት አዛውንት የሚገዟቸውን ቤቶች ለማደስም ምንም ወጪ ማውጣት አይፈልጉም፤ ለስአታት አድካሚ ስራ ከውነው ገንዘባቸውን መቆጠብ ይመርጣሉ።
ልጅም ሆነ የቅርብ ቤተሰብ የሌላቸው ሄንዝ ከራሳቸው እየሰሰቱ ያጠራቀሙትን ሃብት ለማን እንደሚያወርሱት ሲጠየቁ “እስካሁን አላሰብኩበትም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ምናልባትም ለተከራዮቼ አወርሳቸው ይሆናል” ማለታቸውም ቤቶቻቸውን ለተከራዩ ሰዎች መልካም ዜና ሳይሆን አይቀርም።