የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አል-ባሽር በሀገሪቱ ፍርድ ቤት የ 2 ዓመት እስር ተፈረደባቸው
የወራት ህዝባዊ አመጽን ተከትሎ በሀገሪቱ ጦር ባለፈው ዓመት ከስልጣን የወረዱት የ75 ዓመቱ አል-ባሽር በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር፣ ዩሮ እና የሱዳን ፓውንድ በቤታቸው ተገኝቷል በሚል ህገወጥ ገንዘብ ይዞ በመገኘት የሙስና ወንጀል ነው ቅጣቱ ዛሬ ታህሳስ 04 ቀን 2012 ረፋድ ላይ የተወሰነባቸው፡፡
እድሜው ከ70 ዓመት በላይ የሆነ ግለሰብ በሱዳን ህግ መሰረት እስር ቤት የማይገባ በመሆኑ አል-ባሽር በተለየ ማህበራዊ ማሻሻያ የማረሚያ ማእከል እንዲቆዩ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡
በካርቱም በነበረው የፍርድ አሰጣጥ ሂደት ወቅት በፕሬዝዳንቱ ወገን ፍርድ ቤት የተገኙ ጠበቆች እና የህግ አካላት ውሳኔውን በመቃወም ከዳኛው ጋር ጸብ ውስጥ በመግባት ከአዳራሹ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ የፕሬዝዳንቱ ተከላካይ ጠበቆች ዳኛውን ፖለቲከኛ እንደሆነ በመጥቀስ ውሳኔውን ፖለቲካዊ እያሉ ሲያጣጥሉ ተሰምተዋል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ወር ከስልጣናቸው በግድ የተነሱት ፕሬዝዳንት አል-ባሽር ከሙስና ወንጀል በተጨማሪ በሌሎች ወንጀሎችም የተከሰሱ ሲሆን በቀጣይነት እንደ አውሮፓውያኑ በ1989 ወደስልጣን የመጡበት የመፈንቅለ መንግስት ክሳቸው ይታያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም ወንጀለኛ ሆነው ከተገኙ ከዛሬው የሁለት ዓመት እስር ብያኔ ጋር ተደምሮ ውሳኔው እንደሚተገበር ነው ዘገባዎች የሚያመለክቱት፡፡
ከስልጣን እንዲነሱ ምክኒያት በሆነው በ2019ኙ ህዝባዊ አመጽ ህይወታቸውን ካጡ ዜጎች ጋር በተያያዘም ሶስተኛ ተጨማሪ ክስ ሊጠብቃቸው ይችላል ተብሏል፡፡
እነዚህ ክሶች ተደማምረው የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ቅጣት ሊያከብዱት እንደሚችሉ ይታመናል፡፡
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ/ICC) ከዳርፉር ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ በዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀለኝነት ክስ መስርቶባቸው ለአመታት በጥብቅ ቢፈልጋቸውም የሀገሪቱ ጦር አሳልፎ እንደማይሰጣቸው አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሀሙስ የፕሬዝዳንት አል-ባሽር ሁለተኛ ባለቤት ዊዳድ ባቢክርም በሙስና ተጠርጥረው ካርቱም ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡