የፌዴራል ዕርቀ ሠላም ኮሚሽን አባላት ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ተወያይተዋል
የፌዴራል ዕርቀ ሠላም ኮሚሽን አባላት ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ ታህሳስ 04 ቀን 2012 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ተወያይተዋል፡፡ የውይይቱ ዓላማም በቀጣይነት አብሮ መሥራት የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እንዳሉት ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ በተፈጠሩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች በሕዝብ ዘንድ ቁርሾዎች ታይተዋል፡፡ ዕርቀ ሠላም የሕዝብን ሠላምና ደኅንነት በዘላቂነት በማረጋገጥ የመንግሥትን የልማት ስትራቴጂ በጥራት እና በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲሁም ዜጎች በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቅሰው በነጻነት እንዲሠሩ ምቹ ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልእኮ በአግባቡ እንዲወጣ ከየክልሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ምክክር እያደረገ መሆኑንም ነው ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል የተናገሩት፡፡ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ትግራይ እና ጋምቤላ ክልሎች ተመሳሳይ ውይይት ተደርጓል፡፡
ዕርቀ ሠላም በባሕሪው አሳታፊ እና የችግርን መሠረት ነቅሎ በማውጣት ላይ ያተኮረ የግጭት መፍቻ ሂደት መሆኑን የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ የጋራ እውነት እንዲኖር፣ ለፍትሕ ሥርዓት አስተዋፅዖ ለማድረግ፣ ለተበዳዮች ዕውቅና ለመስጠት እና የባለፉ ግጭቶችን በማጤን ድጋሜ እንዳይከሰቱ የመከላከያ ርምጃ ለመውሰድ የጎላ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ነው ሎሬት የትነበርሽ የተናገሩት፡፡
በአፍሪካ፣ በአውሮፓና አውስትራሊያ ሀገራትም ‘የአካባቢ ተወላጆች እና መጤ’ ተብለው በሚጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም በተለያዩ ጊዜያት ዕርቀ ሠላም ተግባራዊ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ “የኮሚሽኑ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የክልሎችን ተባባሪነት ይጠይቃል” ያሉት ሎሬት የትነበርሽ የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ኮሚሽኑ የሚያከናወናቸውን ተግባራት በቁርጠኝነት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ አያሌው “አንዱ ቤተኛ ሌላው መጤ፣ ገዳይና ተገዳይ፣ አፈናቃይና ተፈናቃይ፣ በዳይና ተበዳይ፣ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ የመሆን አዝማሚያዎች በስፋት እየተስተዋሉ ነው” ብለዋል፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የችግሩ ተጎጂ ቢሆኑም አማራ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ ሆኖ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
“በመሆኑም ኮሚሽኑ የችግሮችን ምንጭ በማጥናት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በሀገሪቱ ሠላም እና አንድነት እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል” ብለው እንደሚያምኑም አቶ ላቀ ገልጸዋል፡፡ ለኮሚሽኑ በጎ ተግባር የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ትብብር እንደማይለየውም ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የዕርቅ እና የሠላም መድረኮች እየተደረጉ መሆኑም ለዚህ አጋዥ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡
ምንጭ፡- አብመድ