በጥምቀት በዓል ላይ ወንጀል ለመፈፀም የተዘጋጁ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ገለጸ
ለወንጀል ተዘጋጅተዋል የተባሉ 3 ተሸከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል
በቀጥታ በወንጀል ተሳታፊ የሆኑ 205 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በህብረተሰቡ ጥቆማ መነሻነት ባደረገው ጥናት በጥምቀት በዓል ላይ ወንጀል ለመፈፀም ተዘጋጅተው የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በቀጥታ በወንጀል ተሳታፊ የሆኑ 205 ተጠርጣሪዎችን" በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል፡፡"
ተጠርጣሪዎቹ ቀደም ሲል በደረሱት ጥቆማዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ "ለወንጀል ድርጊት ያዘጋጁት ሰነድ አልባ ሦስት ተሽከርካሪዎችም" ተይዘዋል፤ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይም የምርመራ መዝገብ በማደራጀት ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ኮሚሽኑ በአስሩም ክ/ከተማ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማና ይህንንም ጥቆማ መሰረት አድርጎ ባደረገው የቁጥጥር ተግባራት በዓሉ "በሠላም እንዳይከበርና ሁከት እንዲነሳ" ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ ከሦስት መቶ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ግለሰቦቹ ለወንጀል መፈፀሚያነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን ጨምሮ ህገ ወጥና ፈቃድ የሌለው ሽጉጥም ይዘው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡
ህብረተሰቡ ማንኛውንም ጥቆማ በኮሚሽኑ የነፃ ስልክ መስመር 991 እንዲሁም በ0111 11 01 11 በመደወል ማድረስ እንደሚችልም አሳውቋል፡፡