በአዲስ አበባ ለሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የነዳጅ ድጎማ ሊደረግላቸው ነው
የድጎማው ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎች እስከ ሚያዝያ 30 ድረስ አቅጣጫ ጠቋሚ ወይም GPS የግድ ማስገጠም አለባቸው ተብሏል
የነዳጅ ድጎማው የፊታችን ሀምሌ ይጀመራል ተብሏል
በአዲስ አበባ ለሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የነዳጅ ድጎማ ሊደረግላቸው መሆኑ ተገለፀ።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለአል ዐይን በላከው መግለጫ፤ በከተማው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሸከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ማድረግ በሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የድጎማ ስርዓቱ በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ቢሮው ገልጿል።
በድጎማ ስርዓቱ GPS እንዲገጠም መደረጉም የትራንስፖርት ስምሪቱን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ቁጥጥሩን ለማሳለጥ ዕድል ይፈጥራል።
ድጎማው ከሀምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆንም የቢሮው መግለጫው ያስረዳል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጐማ አፈፃፀም ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን የገለጸ ሲሆን፤ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውይይት መደረጉም ተገልጿል።
የነዳጅ ድጎማው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ህብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ በታሪፍ እና በስምሪት ቁጥጥር ላይ የተመሠረተ መለስተኛ፣ መካከለኛ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ተሸከርካሪዎችን ይመለከታልም ተብሏል።
በዚህም መሰረት በመዲናዋ የህዝብ የትራንስፓርት አገልግሎት የሚሠጡ የመንግሥትና የግል አውቶቡሶች፣ የሳሎን ታክሲዎችን ሳይጨምር በከተማ ውስጥና በከተሞች መካከል የህዝብ የትራንስፓርት አገልግሎት የሚሠጡ ኮድ 1 እና ኮድ 3 ሚኒባስ (አዲስ አበባ ውስጥ የተመዘገቡ) ተሽከረካሪዎችን እንደሚያካትት ቢሮው አስታውቋል።
ሆኖም ግን በመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ በግል እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሠራተኛ አገልግሎት እንዲሁም በግል ትምህርት ቤቶች የተማሪ አገልግሎት የሚሠጡ ድጎማው አይመለከታቸውም ተብሏል።
በድጎማ ስርዓቱ የተመዘገቡ ተሸከርካሪዎች እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜ ውስጥ GPS መግጠም አስገዳጅ ነው ተብቧል።
እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸው እስከ ገንቦት 30/2014 ዓ.ም የተሸከርካሪዎች መረጃ ወደዳታ ቤዝ የማስገባት ስራ ይሰራል ብለዋል።
በመሆኑም በመዲናዋ በህዝብ ትራንስፖርት የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን የሚመለከቱ አጠቃላይ መረጃዎች በአስር ቀናት ተደራጅተው ለቢሮው እንዲላኩለት ጠይቋል።