የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 90 ዶላር መድረሱ ተገለፀ
ድፍድፍ ነዳጅ አሁን ላይ እየተሸጠበት ያለው ዋጋ ከ7 ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል
በ2022 የ1 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 100 የአሜሪካ ዶላር ሊደርስ እንደሚችልም ተንበያዎች ያመለክታሉ
የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከፈረንጆቹ 2014 ወዲህ በዓለም ገበያ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ላይ መሆኑ ተሰምቷል።
በኒው ዮርክ የነዳጅ ዋጋ የ2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎም አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከሰባት ዓመትት ወዲህ በ90 ዶላር እየተሸጠ መሆኑን ብሉምበርግ ዘግቧል።
የዓለም የነዳጅ ዋጋ በዚህ ደረጃ ጭማሪ የተያየው በሩሲያ እና በየክሬን መካከል የተፈጠረውን ውጥረት እንደሆነም ተነግሯል።
ውጥረቱን ተከትሎም የሩሲያ እና የምዕራባውያን ፍጥጫ እንዲሁም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን ለመውረር ትእዛዝ ከሰጡ የተናጥል ማዕቀብ ይጠብቃቸዋል ማለታቸው ተከትሎ የሚፈጠው አለምገባባት የነዳጅ አቅርቦት ላይ እጥረት ሊፈጠር ይችላል የሚለው ስጋትም ለወጋው ጭማሪ በምክንያትነት ተቀምጧል።
በየመን የሚንቀሳቀሱት የሁሲ አማፅያን የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን ባሳለፍነው ሳምንት ያደረሱትን የሽብር ጥቃት እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ በተደጋጋሚ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶችም ለነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ምክንያት ሆነዋል ተብሏል።
እንደ አዲስ እያንሰራራ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም የነዳጅ ዋጋ አንዴ ዝቅ አንዴ ከፍ እያደረገው መሆኑም ይታወቃል።
አሁን ያለው የዓለም የገበያ ሁኔታ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 100 የአሜሪካ ዶላር ሊደርስ እንደሚችልም ተንበያዎች ያመለክታሉ።