የጋዜጠኞቹ ጉዳይ ዛሬ ከሰዓት ያልታየው ዳኛ ባለመኖሩ ነው ተብሏል
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ መዓዛ መሀመድና እና ሰለሞን ሹምዬ እያንዳንዳቸው በ 10ሺ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ወስኖ ነበር፡፡
ምንም እንኳን ፍርድ ቤት ጋዜጠኞቹ በዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ቢሰጥም ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጠን ይገባል ብሎ ጠይቋል፡፡
ጋዜጠኞቹ ፍርድ ቤቱ ባዘዘው መሰረት የዋስትናውን ሂደት ያስጀመሩ ቢሆንም ፖሊስ በዋስ እንዳይለቀቁ ሲል በመጠየቁ ከእስር ሳይለቀቁ ቀርተዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ ዛሬ አራት ሰዓት ላይ በታየው ችሎት በዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ የተሰጠ ቢሆንም ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቁ፤ ጉዳዩ ከሰዓት መልስ ተቀጥሮ ነበር፡፡
ይሁንና ዳኛ ባለመኖሩ ምክንያት የጋዜጠኞቹ ጉዳይ ነገ እንደሚታይ የአል ዐይን የመረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ የመዓዛ መሀመድ እና የሰለሞን ሹምዬን ጉዳይ ነገ ረቡዕ ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ/ም ጠዋት የሚመለከት ይሆናል፡፡
የፍትሕ መጽሔት ማኔጅንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ተመስገን "ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በዩ ቱብ ኢንተርቪዎችን በመስጠት ቀስቅሷል" የሚል ክስ የቀረበበት ሲሆን ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ ነው፡፡
በሌላ በኩል ችሎቱ የመስከረም አበራ እና የጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስንም ጉዳይ ዛሬ ተመልክቶ ነበር፡፡ ሆኖም ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን መጠየቁን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ስድስት ተጨማሪ ቀናትን ፈቅዷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችንና ማህበረሰብ አንቂዎችን እያሰረ ነው በሚል ትችቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ም የመንግስት ድርጊቱን ኮንኗል፡፡
መንግስት ግን ተቺዎችን እያሰረ አለመሆኑን በመጥቀስ እየሰራ ያለው ህግ የማስከበር ስራ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል፡፡