የዳኞችን ስራ ታቀላለች የተባለችው ማይክሮቺፒ የተገጠመላት የአዲዳስ ኳስ
በኳሷ መሀል ላይ የምትገጠመው ማይክሮቺፕ በሰከንድ 500 እንቅስቃሴዎችን በመመዝገብ ለዳኞች ትልካለች ተብሏል
ማይክሮቺፕ የተገጠመላት ኳስ በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ጥቅም ላይ ትውላለች
በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ማይክሮቺፕ የተገጠምላት ኳስ እንደሚያቀርብ አዲዳስ አስታውቋል።
የጀርመኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች እንደገለጸው ቻርጅ የሚደረግ ባትሪ ያላት ማይክሮቺፕ በሰከንድ 500 እንቅስቃሴዎችን በቪዲዮ ዳኝነት ለሚሰጡት ትልካለች።
ይህም ዳኞች ኳስ በእጅ ተነክቷል ወይስ አልተነካም የሚል ውሳኔን ጨምሮ ሌሎች ጥፋቶች ሲፈጸሙ ፈጣን ውሳኔ እንዲሰጡ ያስችላል ነው የተባለው።
በእግርኳስ ኳስ ወደ እጅ፤ እጅ ወደ ኳስ፤ የተቀናቃኝን ግብ የማስቆጠር እድል የማምከን እድል እና ተያያዥ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ተጫዋቾችን ከዳኞች ጋር ሲያነታርክ ይታያል።
የአዲዳስ አዲስ ኳስም ተጫዋቾች ከኳስ ጋር ያላቸውን ንክኪና እንቅስቃሴ እየመዘገበች ወዲያውኑ ጨዋታውን በቪዲዮ ለሚዳኙት መላኳ የመሃል ዳኛውን ውሳኔ ለፍትሃዊነት ያቀርበዋል ተብሏል።
ማይክሮቺፗ በሰከንድ ከ500 በላይ እንቅስቃሴዎችን የመመዝገብ አቅም እንዳላት ነው አዲዳስ ያስታወቀው።
አዲዳስ በጀርመን በሚካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ የሚያስተውቃት ባለማይክሮቺፕ ኳስ የኦፍሳይድ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሂደት ጥቅም ላይ ትውላለችም ተብሏል።
ኳስ መሀል ላይ የምትገጠመው ማይክሮቺፕ በ2022ቱ የኳታር የአለም ዋንጫ ከጨዋታ ውጭ ወይም ኦፍሳይድ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሂደት ጥቅም ላይ መዋሏንም ስካይ ኒውስ አስታውሷል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዳኞች የእጅ ንክኪ ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን በቪዲዮ ዳኝነት (ቫር) በመታገዝ ያሳልፋሉ።