የእስያ እግርኳስ ማህበር ለሳኡዲ ድጋፉን ሰጥቷል
ሳኡዲ አረቢያ የ2034ቱን የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ተቃርባለች።
አውስትራሊያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ከሳኡዲ ጋር አልፎካከርም ማለቷን ተከትሎ ነው ሪያድ ከ11 አመት በኋላ የአለም ዋንጫውን የማዘጋጀት እድሏ ሰፍቷል የተባለው።
የአለም እግርኳስ ማህበር (ፊፋ) ሀገራት ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ዛሬ ይጠናቀቃል።
በዚህም ሪያድ ብቸኛዋ ተፎካካሪ ሆናለች።
የ2026ቱን የአለም ዋንጫ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በጥምረት ያዘጋጃሉ። የ2030ውን ደግሞ ሞሮኮ፣ ፖርቹጋል እና ስፔን እንዲያዘጋጁት ተመርጠዋል።
ፊፋ የ2034ቱ የአለም ዋንጫ በእስያ ወይም ኦሽኒያ እንዲካሄድ መወሰኑ አይዘነጋም።
ብቸኛዋ ውድድሩን ለማዘጋጀት ተፎካካሪዋ ሳኡዲ አረቢያም ይህን አለማቀፍ ውድድር እንድታዘጋጅ ፈቃድ እንደሚሰጣት ይጠበቃል።
የእስያ እግርኳስ ማህበር ለሳኡዲ ድጋፉን መስጠቱን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
ሪያድ ከ2018 ጀምሮ የእግርኳስ ውድድሮችን፣ እንደ ፎርሙላ 1፣ ጎልፍ እና ቦክስ ውድድሮችን አስተናግዳለች።
የሀገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር ልኡል አብዱላዚዝ ቢን ቱርኪ ቢን ፋይሰል ውድድሩን ማዘጋጀት ሀገሪቱ ለእግር ኳስ ያላትን ፍቅር የምታሳይበት ነው ብለዋል።
የሳኡዲ ክለቦች ክርስቲያኖ ሮናልዶን ጨምሮ በርካታ የአለማችን ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾችን አስፈርመው ሊጉ እየተነቃቃ ነው።
የአውሮፓ ክለቦች ከሪያድ ክለቦች የሚለቀቀው አጓጊ ገንዘብ ተጫዋቾችን እያስኮበለለ ነው በሚል ይወቅሳሉ።
የሀግሪቱ ልኡል አልጋወራሽ ሞሀመድ ቢን ሳልማን ግን “በእግርኳስ ላይ የምናወጣው ወጪ በጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታችን (ጂዲፒ) ላይ የ1 በመቶ እድገት ካመጣ ገንዘብ ማውጣታችን እንቀጥላለን” ማለታቸ ይታወሳል።