የአቡ ዳቢ ናሽናል ኦይል ኩባንያ፤ ከውድ የዩኤኢ ታዋቂ የንግድ ምልክቶች ቀጥር አንዱ ሆኖ ተመረጠ
ኩባንያው በዩኤኢ 1ኛ ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ካሉ ብራንዶች ደግሞ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል
ADNOC ለተከታታይ 4ኛ ጊዜ ነው በታዋቂ የንግድ ምልክትነት የተመረጠው
የአቡ ዳቢ ናሽናል ኦይል ኩባንያ (ADNOC) ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ታዋቂ የንግድ ምልክቶች ቀጥር አንዱ ሆኖ ተመረጠ፡፡
ADNOC በታዋቂው ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማት መዛኝ እና ስትራቴጅካዊ የማማከር አግልግሎት ሰጪ ድርጅት ‘ብራንድ ፋይናንሺያል’ ነው ከዩኤኢ ቀዳሚ ሆኖ የተመረጠው፡፡
በቀዳሚ ታዋቂና ውድ የንግድ ምልክትነት (ብራንድ) ሲመረጥ ለተከታታይ 4ኛ ጊዜ ነው፡፡
የ12 ነጥብ 76 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳለው የሚገመተው የኩባንያው ብራንድ በዚህ አመት ብቻ የ19 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
ከፈረንጆቹ 2017 ወዲህ ከ174 በመቶ በላይ አጠቃላይ እድገት ማሳየቱንም ነው የ‘ብራንድ ፋይናንሺያል’ ሪፖርት የሚጠቁመው፡፡
“የኩባንያው ብራንድ በዩኤኢ 1ኛ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ካሉ ብራንዶች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን በአለም አቀፍ የነዳጅ እና ጋዝ ኩባንያዎች ከፍተኛ ደረጃ ከተሰጣቸው 10 ብራንዶች 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል” ሲልም አክሏል ሪፖርቱ፡፡
የኩባንያው ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር እና ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑትን ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃብርን (ዶ/ር)ም በዩኤኢ እና በመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዋና ስራ አስፈፃሚዎች መካከል አንደኛ አድርጎ አስቀምጧል ‘ብራንድ ፋይናንሺያል’፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው የዩኤኢ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
በዩኤኢ በኢነርጂ መስክ ተጨባጭ ለውጥን ለማስመዝገብና በዘርፉ የሃገራቸውን አበርክቶ ለማሳደግ እየሰሩ ይገኛሉም ተብሏል፡፡
ኩባንያው በዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ኃይል ሊያመነጭ በሚችልባቸው አዳዲስ የኢነርጂ ስትራቴጂዎች ዙሪያ ቅድሚ ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡
ባለፉት 12 ወራት ብዙ ስኬቶችን በማስመዝገብም በንጹህ እና ታዳሽ እንዲሁም በሃይድሮጂን ሃይል ዘርፍ ደረጃውን ማስጠበቅ ችሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በዩኤኢ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡