“አድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን ለነጻነታቸው ብቻ አይደለም የተዋጉት”
“እንቆቅልሹ የቱ ጋር ነው ካልን አድዋ ላይ የተመታው ዘረኝነት በአድዋ ሰዎች አንሰራርቶ እዚህ መምጣቱ ነው”- አበባው አያሌው፣ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ
“ታሪክን አጣሞ ለፖለቲካ የመጠቀሙ ነገር አሁንም አልቀረም፡፡ ይሄ ደግሞ አይጠቅምም፤ የትም አያደርስም፤ ህወሓትንም የትም አላደረሰም”
125ኛው የአድዋ ድል በዓል ዘንድሮ ለየት ባለ ሁኔታ እናከብረዋለን በሚል “ዓድዋ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት አርማ” በሚል መሪ ቃል ወሩን (የካቲትን) ሙሉ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ነው የሚከበረው፡፡ በፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የሚመራ ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴም አከባበሩን ያስተባብረዋል ተብሏል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከሳምንታት በፊት በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በነበረው “ቱባ-ወግ” መድረክ ላይ “በአድዋ ጦርነት ያሸነፍነው ዘረኝነትን ነው” ካሉት ከታሪክ መምህርና ተመራማሪው የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር) ጋር በዓሉን በተመለከተ ቆይታ አድርጓል፡፡
በቆይታው ከድሉ አንድምታ እና የአከባበር እውነታዎቹ ጋር የተያያዙ ዓይነተ ብዙ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ የቆይታውን የመጀመሪያ ክፍል እንዲህ ባለ መልኩ አሰናድተነዋል፡፡ ያንብቡት፡፡
አል ዐይን ፡ “ቱባ-ወግ” ላይ በአድዋ ጦርነት ያሸነፍነው ዘረኝነትን ነው!! ብለዋል ምን ለማለት ነው?
አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር)፡ በአብዛኛው አድዋን የምንዘክረው ወትሮም ሆነ አሁን በቅኝ ገዢ ኃይል ላይ ወታደራዊ ድል ያገኘንበት አድርገን፤ ለነጻነታችንና ለሉዓላዊነታችን መከበር ብቻ አጽንኦት ሰጥተን ነው፡፡ ግን የአድዋ ድልን በሁለንተናው ሰፋ ባለ መንገድ ትንትነነው ተመልክተነውም አናውቅም፡፡
አውሮፓ አፍሪካውያንን ቅኝ ለመግዛት ሲመጣ በጥቁር ዘር የበታችነት አምኖ በዘር በቀለም ከፋፍሎ ሊገዛ ነው፡፡ ሁሉም ቅኝ ሲገዛ በዚህ ዘረኝነት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ስለዚህ አድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት ብቻ አይደለም የተዋጉት፡፡ ለነጻነታቸውማ ወትሮም ሲዋጉ ነበር፡፡ ከማሃዲስቶች፣ ከደርቡሾች እና ከግብጾች ጋር የተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
የአድዋው ከነጻነት የዘለለ ነበረ፡፡ ከነጻነታችን ከሉዓላዊነታችን ባሻገር ያ ቅኝ ገዢ ኃይል ይዞት የመጣውን የዘረኝነት አስተሳሰብ እዛው አድዋ ላይ ድባቅ የተመታበት ነው፡፡ ሰፋ አድርገን ስለማናየው እንጂ ትልቁ ነገር ይሄ ነው፡፡
አፍሪካውያን ነጻነታቸውን ሲያገኙ የኮሩት ለምንድነው? አንደኛው ትልቁ ነገር ነጻ መንግስት መሆናቸው አይደለም መብታቸውን ማግኘታቸው ነው፡፡ እኩልነታቸውን ማስከበራቸው ነው፡፡
አል ዐይን ፡ ታዲያ አሁን ዘረኝነት ምን አግኝቶ ሊሰለጥን ቻለ?
አበባው ፡ አንድ እንቆቅልሽ የሆነ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለረዥም ዘመናት እስከ 1983 ዓ/ም ድረስ ምንም የፖለቲካ ልዩነት አስተሳሰብምይኑረን ተዋግተንም እርስበእርስ ተጣልተንም እናውቃለን፡፡ የሰገሌ ጦርነት እርስበእርስ አለመግባባት ነው፤ የእምባቦ ጦርነትም እንደዚያው ነው፡፡ ኢህአፓ እና ደርግ እርስበርስ ተገዳደሉ ማለት በፖለቲካ ነው፡፡ እነዚህ በታሪካችን የነበሩ ናቸው፡፡
ከ1983 በኋላ ግን ፖለቲካው የብሄርን መልክ መላበስ ጀመረ፡፡ ጥያቄው ሲነሳ ከተማሪዎች ንቅናቄ ከፖለቲካው ጋር ተያይዞ ነበረ፡፡ ያ ሲሆን ግን ጥያቄው በአብዛኛው ወዲያው በአብዮቱ መፍትሄ አግኝቷል፡፡
በፊውዳል ስርዓቱ የነበረው ጭቆና መሬት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እና የገጠር መሬት አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ ብሄር ተለይቶ አማራን ይመለከታል ኦሮሞውን አይመለከትም አልተባለም፡፡
አብዮቱ “መሬት ላራሹ”በሚል ባመጣው ለውጥ የብሄርን ነገር ፈቶት ሲያልፍ ጫካ የገቡት ደግሞ 17 ዓመት ሙሉ እዛው የብሄርን ነገር ሲያመነዥኩ ቆዩ፡፡ ከመጡ በኋላ ‘እውነት የብሄር ጥያቄ አሁን ተገቢ ነው አይደለም? አለ ወይስ የለም? ’ ብለው እንኳ አልተመለከቱትም፡፡ በዚያው ከተማሪዎች ንቅናቄ ቆንጽለው በዋለልኝ መኮንን ከወሰዷት ተነሱና ብሄርን የፖለቲካ ስርዓቱ ዋነኛ ነገር አደረጉት፡፡ ሁሉን ነገር በጣም አጦዙት፡፡
ይሄ ስር እየሰደደ ወደ ህብረተሰቡ ማህበራዊ ግንኙነት ከዚያ አልፎ ሃይማኖት ውስጥ ተቋማት ውስጥ ገባ፡፡ የብሄርን ቅኝት በየትምህርት ቤቱ በየማህበራዊ መድረኩ በየቦታው እየሰማ ያደገ ትውልድ ደግሞ አለ፡፡ እና አሁን አንድ ጥያቄ ሲነሳ ትልቅ ነገር ሆኖ ወዲያውኑ የፖለቲካ መልክ የሚላበሰው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
እንቆቅልሹ የቱ ጋር ነው ካልን አድዋ ላይ የተመታው ዘረኝነት በአድዋ ሰዎች አንሰራርቶ እዚህ መምጣቱ ነው፡፡
አል ዐይን ፡ ፖለቲካ እንዴት ባለ መንገድ ከታሪክ ላይ እጁን ያንሳ?
አበባው ፡ ታሪክ ከተፈጥሮ ከሰው ሃብት ያልተናነሰ ትልቅ ሃብት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሃገር ታሪክ የሚያስጠናው የሚያስጽፈው በተለያዩ መደበኛ እና ኢ-መደበኛ መንገዶች እንዲተረክ የሚያደርገው ሃብት ስለሆነ ነው፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ ታሪክ ለሃገሪቱ አንድነት፣ ለፖለቲካ ጥንካሬ፣ ለሉዓላዊነት ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ነገር ግን የብሄር ፖለቲካ መቀንቀን ሲጀምር አንዱ አንዱን በጥርጣሬ የሚያይበት፤ የማይተባበርበት ሁኔታ ሲፈጠር ታሪክን እንደ አንድ መሳሪያ ተጠቀሙት፡፡
በታሪካችን እርስበርሳችን የተጣላንባቸው ጊዜዎች ይኖራሉ፡፡ ይሄ ደግሞ በማንም ሃገር ታሪክ አለ፡፡ ያ እንዳለ ሆኖ ግን ከተጋጨንባቸው ይልቅ በአንድነት የቆምንባቸው ዘመናት ይበልጣሉ፡፡ ማህበራዊ ትስስራችንን የሚያጎሉ በርካታ ታሪኮች አሉ፡፡ የባህል ውርርሳችንና ሌሎችንም መስተጋብሮቻችንን የሚያጎሉ ታሪኮች አሉን፡፡ እነዚህን እንደ አድዋ ትልቅ ብሄራዊ አንድነትን የሚያመጡ ነገሮችን መተው ስለተፈለገ እንጂ፡፡
ሁለተኛ አንዱ ብሄር በሌላኛው ሆን ተብሎ እንደተወጋ ተደርጎ የታሪክ ክስተቶችንና ሁነቶችን እየመዘዙ እያወጡ በሚዲያውም በምኑም ሆን ብለው ማሰራጨት ነው የጀመሩት፡፡ ለምሳሌ አኖሌ፣ ጨለንቆ፡፡ እንደዛማ ከሆነ ለምን አኖሌ እና ጨለንቆን ብቻ ማንሳት ያስፈልጋል የአጼ ዮሐንስ የጎጃም ዘመቻ፣ የሰገሌ ጦርነትስ ለምን አይነሳም? ወሎና ሸዋ ሲጣላ ሊኖር ነው ማለት ነው? በዚህ እምባቦስ አለ አይደለም ሚኒሊክና ንጉስ ተክለሃይማኖት የተዋጉበት? ለፖለቲካ ግብዓታቸው የምትሆነዋን ነገር ያቺን እያነሱ እንዲቀነቀን ነው ያደረጉት፡፡ ይሄ ፖለቲካው ታሪክን ለግብዓትነት ተጠቀመበት በተዛባ መንገድ ማለት ነው፡፡ ያ ትልቅ ችግር ፈጠረ፡፡
ከዚያ ውጭ ደግሞ በብሄራዊ ደረጃ ትልቅ የሃገር ኩራት የሆኑ ዜጎችንም እንደዚሁ አወዛጋቢ ማድረግ፤ ለምሳሌ አጼ ሚኒሊክ፡፡ ተወደደም ተጠላም የኢትዮጵያ ንጉስ ናቸው፡፡ በዘመናቸው ኢትዮጵያን በብዙ መንገድ ታላቅ አድርገዋታል፡፡ የአድዋን ድል ጨምሮ ማዘመኑን ብንወስደው ተቋማትን ብንወስድ ባቡሩን ብንል፣ ግዛት ማስፋፋትን፣ ራሱ አሁን ያለውን የኢትዮጵያን ድንበር ገፍቶም ምንም ብሎ የማስከበሩ ነገር በእርሳቸው የተፈጸመ ነው፡፡ ግን ያ ሁሉ ይተውና ‘ሚኒሊክ ጨፍጫፊ ነው አይደለም ’ እዚያ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይደረጋል፡፡
ሁለተኛ ደግሞ እነዚህን ሰዎች በኢትዮጵያዊ እይታ ሳይሆን በብሄር አቁማዳ መክተት፡፡ ለምሳሌ የሚኒሊክ ኢትዮጵያዊነት ቀርቶ አማራ ብቻ ይሆናል፤ አጼ ዮሃንስ በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስትነታቸው ሳይሆን በትግሬነታቸው ብቻ እንዲታዩ ማድረግ፤ ከዚያ ወርዶ ወርዶ በላይ ዘለቀ ‘ጎጃሜ ነው ወሎዬ ነው’ ወደ ሚል ክርክር መግባት፡፡ እንዲህ እየተደረገ ታሪክ ዋና የመጨቃጨቂያ እና የህዝብ መከፋፈያ ተደረገ፡፡
አሁን እነዚህን ነገሮች ለመገንዘብ የሚችሉ ፖለቲከኞች ስለመጡ በተለይ በመንግስት በኩል እነዚህ ፉርሽ መደረጋቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ግን አሁንም ከዚያ አልተላቀቅንም፡፡ ምክንያቱም በየማህበራዊ ሚዲያው በአንዳንድ ፖለቲከኞችም ዘንድ ስንመለከት ታሪክን የፖለቲካ መጠቀሚያ የማድረጉ ነገር ብዙም አልቀረም፡፡ ያ ደግሞ ፖለቲከኞቹን የትም አያደርስም፡፡ ህወሓትን የትም አላደረሰም፡፡ ይሄን የሚያቀነቅኑትም የትም ሊደርሱ አይችልም፡፡ ጎበዝ ፖለቲከኛ ማለት አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መዝኖ ካለፈውም ሊማር ይችላል የወደፊቱን መትለም ነው፡፡ ተምረን እንለፍበት፡፡