አድዋ መታሰቢያ ሙዚየምን ለመጎብኘት 150 ብር መክፈል ግዴታ ነው ተባለ
ሙዚየሙ ከነግ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል
ኢትዮጵያ ከ128 ዓመት በኋላ ለአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መስራቷ ይታወሳል
አድዋ መታሰቢያ ሙዚየምን ለመጎብኘት 150 ብር መክፈል ግዴታ ነው ተባለ፡፡
ኢትዮጵያ ከ128 ዓመት በፊት ለተካሄደው የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ድል ያደረገችበት የአድዋ ድል ሙዚያምን ከሶስት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ በይፋ ማስመረቋ ይታወሳል፡፡
ከ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ይህ ሙዚየም ከነገ መጋቢት ስድስት ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት ይህንን ሙዚየም ለመጎብኘት በግለሰብ ደረጃ 150 ብር መክፈል ግዴታ ሲሆን ለተማሪዎች 75 ብር እንዲሁም ለልዩ ልዩ ጎብኚዎች ደግሞ 500 ብር ዋጋ ተተምኖለታል፡፡
ጎብኚዎች ሙዚየሙን መጎብኘት የሚችሉት ከጠዋት 2:30 እስከ አመሻሽ 11:30 ሰዓት ድረስ እንደሆነም ከመታሰቢያ ሙዚየሙ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
ለሙዚየሙ ከተቀመጡ ማስታወሻዎች መካከል ለድሉ አስተዋጽኦ ያደረጉ የጦር መሪዎች መታሰቢያ ሀውልት እና ተቋማት ስያሜ ባለፈ የራሱ ሙዚየም ሳይሰራለት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን በአዲስ አበባ በተለምዶ ፒያሳ አካባቢ አድዋ ሙዚያም ተሰርቶለታል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የተሰራው ይህ ሙዚየም ምን ያህል ገንዘብ ወጪ እንደተደረገበት መንግስት በይፋ ከመናገር ቢቆጠብም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሙዚየሙ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ዘግቧል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ታከለ ኡማ ግንባታው የተጀመረው ይህ ሙዚየም የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ተመርቋል፡፡
በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ሙዚየም ከምድር በታች ሁለት ደረጃዎችን ጨምሮ 5 ወለል እና 8 በሮች አሉት።
ስምንቱ በሮችም የምሥራቅ ጀግኖች በር፣ የምዕራብ ጀግኖች በር፣ የሰሜን ጀግኖች በር፣ የደቡብ ጀግኖች በር፣ የፈረሰኞች በር፣ የአርበኞች በር፣ የፓን-አፍሪካኒዝም ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።
ኢትዮጵያ ከ128 ዓመት በኋላ ለአድዋ ድል መታሰቢያ የሰራችው ሙዚየም ምን የተለየ ነገር ይዟል?
ቅኝ ለመግዛት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው የጣልያን ጦር ጋር በተደረገው ጦርነት ለአድዋ ድል መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉ የጦር መሳሪያዎች፣ ወኔ መቀስቀሻ መሳሪያዎች፣ ለጦርነቱ መነሻ የሆኑ ስምምነቶች እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ሁሉ በሙዚየሙ ውስጥ ለእይታ ቀርበዋል፡፡
በሙዚየሙ ውስጥ የጸረ ቅኝ ግዛት ጦርነቱ በድል እንዲቋጭ ያደረጉ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ጀምሮ የጦር መሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ እንስሳት እና ሌሎችም ተሳታፊዎች መታሰቢያ ተሰርቶላቸዋል፡፡